Quantcast
Channel: Kalkidantube
Viewing all articles
Browse latest Browse all 3774

‹‹በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የአውራ ፓርቲ ሥርዓት ቦታ የለውም›› ዶ/ር አበራ ደገፋ፣ የሕገ መንግሥት ኤክስፐርት

$
0
0

ዶ/ር አበራ ደገፋ የሕገ መንግሥት ኤክስፐርት ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ዶ/ር አበራ በሕገ መንግሥት ጉዳዮች ላይ በርካታ ሥራዎችን አሳትመዋል፡፡

ከቀናት በፊት ነሐሴ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በሥራ ላይ ከዋለ 20ኛ ዓመቱን በደፈነው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት፣ በተለይም ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን በተሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣንና ከአተገባበሩ ጋር በተገናኙ ጉዳዮች ላይ ሰለሞን ጎሹ ከዶ/ር አበራ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

kalkidantube.com53

ሪፖርተር፡- ሕገ መንግሥቱ በሥራ ላይ ከዋለ በኋላ በአስተዳደር ጉዳይ ላይና በዜጎች አስተሳሰብ ላይ ምን ዓይነት መሠረታዊ ለውጥ አምጥቷል?

ዶ/ር አበራ፡- ሕገ መንግሥቱ ሲወጣ ብዙ ነገሮች ይለወጣሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡ ቃል የገባቸውን ነገሮች ወደ ተግባር ይለውጣል ተብሎ ተስፋ ተደርጎ ነበር፡፡ ከ20 ዓመት በኋላ ግን የተጠበቀውን ያህል ሕገ መንግሥቱ ለውጥ አላመጣም፡፡

ሪፖርተር፡- የሕገ መንግሥቱ ተግባራዊነት የተገደበበትን ምክንያት አንዳንዶች ከዲዛይን ጋር ሲያገናኙት ሌሎች ግን ከፖለቲካ ልሂቃኑ በጎ ፈቃድ ጋር ያዛምዱታል፡፡ ለእርስዎ ቁልፍ የችግሩ ምንጭ ምንድነው?

ዶ/ር አበራ፡- ዲዛይን በተደረገው የተቋማት ሚናና የግለሰቦች ተፅዕኖ መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት አለ፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ የግለሰቦች ሚና ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን ከዲዛይንም አንፃር ሕገ መንግሥቱ ክፍተቶች አሉበት፡፡ ለምሳሌ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ብንወስድ ይሠራቸዋል ተብሎ የተሰጡትን ተግባራት በስኬት ለመፈጸም በሚያስችል መልኩ ነው ወይ የተዋቀረው የሚለውን ብንመለከት፣ ያ ዓይነት ሥልጣን እንዳልተሰጠው ማየት ይቻላል፡፡ ምክር ቤቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚታቀፉበት ነው፡፡ ነገር ግን የእነዚህን ቡድኖች መብት ለማስጠበቅ የሚያስችል አወቃቀር የለውም፡፡ የመጀመሪያው ችግር ሕግ የማውጣት ሥልጣን የሌለው መሆኑ ነው፡፡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር ሲነፃፀር ሥልጣን የለውም ማለት ይቻላል፡፡ በፌዴራል መንግሥት አወቃቀር የላይኛው ምክር ቤት የፌዴሬሽኑን መሥራች አባላት መብት ያስጠብቃሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ ክልሎችና ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አንድ አይደሉም፡፡

በእርግጥ እንደ ኦሮሚያ ባሉ ክልሎች ሁለቱ ተደራርበው ይገኛሉ፡፡ አንቀጽ 39(3) ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት አለው ይላል፡፡ ይሁንና የክልልነት ደረጃ የሌላቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ይህን መብት ለመጠቀም ይቸገራሉ፡፡ ሌላው የዲዛይን ችግር ሕገ መንግሥቱ ራሱ ለፌዴራል መንግሥቱ አብዛኛውን ሥልጣን የሰጠና ለክልሎች ደግሞ የተወሰኑትን የሰጠ መሆኑ ነው፡፡ የፋይናንስና የተፈጥሮ ሀብትን የመጠቀም ሥልጣን ለክልሎች የተሰጠው በተወሰነ መልኩ ነው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተሰጠውን ሥልጣን ነው ሊያስከብር የሚችለው፡፡ ባልተሰጣቸው ሥልጣን ላይ ሊሠራ አይችልም፡፡

ሪፖርተር፡- የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከማንነት ጥያቄ፣ ከግጭት አወጋገድ፣ ከጋራ ገቢና ከክልሎች ድጎማ፣ ከፌዴራል መንግሥቱ በክልል ጣልቃ ከመግባት ጋር በተያያዙና በመሰል ጉዳዮች ላይ በርካታ ሥልጣኖች ተሰጥቶታል፡፡ የተቋሙ አፈጻጸም ደካማ የሆነው በሥልጣን እጦት ሳይሆን በፖለቲካ ቁርጠኝነት ማነስ ነው በማለት የሚቀርበውን ክርክር እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር አበራ፡- እነዚህም ሥልጣኖች ቢሆኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ብቻውን የሚጠቀማቸው አይደሉም፡፡ ለምሳሌ ያህል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62(9) ላይ ‘ማንኛውም ክልል ይህን ሕገ መንግሥት በመጣስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ያዛል’ በማለት ለምክር ቤቱ ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡ በነገራችን ላይ እንዲገባ ያዛል እንጂ በሚወጣበት ሁኔታ ላይ ውሳኔ ስለመስጠት ሕገ መንግሥቱ ምንም የሚለው ነገር የለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የፌዴራሉ መንግሥት በክልሎች ጣልቃ የሚገባበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣው አዋጅና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ ምክር ቤቱ ብቸኛው ወሳኝ እንዳልሆነ የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ ምክር ቤቱ ሳይጠየቅ የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ የሚገባበት ዕድል ሁሉ አለ፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱን ጠንካራና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥልጣንና ተግባራት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አልተሰጡም፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ በተለይም የአስፈጻሚው አካል ሥልጣን ላይ ገደብና ቁጥጥር በማድረግ ለክልሎች ወይም ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት ጥብቅና በሚቆምበት መልኩ አልተደራጀም፡፡

ሪፖርተር፡- በሕገ መንግሥቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትን የክልል ምክር ቤቶች በራሳቸው ወይም በቀጥታ በሕዝብ እንዲመረጡ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተደንግጓል፡፡ በተግባር ግን ሕዝቡ በምርጫው ተሳትፎ እንዲያደርግ ተደርጎ አያውቅም፡፡ የክልል ምክር ቤቶች ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ወደ ሥራ ከገባ ጀምሮ ተለውጦ በማያውቀው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ተፅዕኖ ሥር ናቸው ተብለው ይታማሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የፖለቲካ አካሄዱ ተፅዕኖ ከዲዛይን ችግር እጅግ የላቀ ነው በማለት የሚከራከሩትን እንዴት ያዩዋቸዋል?

ዶ/ር አበራ፡- የፖለቲካው ምኅዳርና የፓርቲው ሥርዓት የባሰ ችግር ፈጥሯል፡፡ የክልል ምክር ቤቶች በገዥው ፓርቲ ቁጥጥር ሥር ናቸው፡፡ ይኼ ቢለወጥ የተወሰነ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፡፡ ነገር ግን ዋናው ነገር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር (ቬቶ) መብት የሌለው መሆኑ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱንም የሚተረጉመው ጉዳዩ ሲቀርብለት እንጂ በራሱ ተነሳሽነት የክልሎች ወይም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት ተነካ ብሎ አይደለም፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣውን ሕግ ያዘጋጀለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ስለዚህ የራሱንም መብት ማስጠበቅ ያልቻለ ምክር ቤት ነው፡፡ በአጠቃላይ ነፃና ገለልተኛ ተቋም አልሆነም፡፡ አሁን ያለው የአንድ ፓርቲ ሥርዓት ብዙ ነገር አበላሽቷል፡፡ ይሁንና ወደ መድበለ ፓርቲ ሥርዓት ብንሸጋገርም የፌዴራል ሥርዓቱ ውጤታማ እንዲሆን የክልሎች ሥልጣን ሊጨምር ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ዋነኛው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣን ሕገ መንግሥቱን መተርጎሙ ነው፡፡ ባልተለመደ መልኩ ይህ ሥልጣን የተሰጠበት ምክንያት ለእርስዎ አሳማኝ ነው?

ዶ/ር አበራ፡- አገሮች ሕገ መንግሥት ሲያረቁ ከሌሎች አገሮች መማር ቢኖርባቸውም፣ ለራሳቸው ልዩና ተጨባጭ ሁኔታ ትኩረት መስጠትም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይሁንና የፌዴራል የመንግሥት አወቃቀርን የሚከተል ሕገ መንግሥት ሲረቀቅ ሊሟሉ የሚገቡ መሠረታዊ ሁኔታዎች አሉ፡፡ አንደኛው ሁኔታ የክልሎችን ውክልና የያዘው ምክር ቤት ወይ በሕግ ማውጣት ሒደቱ ሊሳተፍ ካልሆነም ውሳኔን በውሳኔ የመሻር መብት ሊያገኝ ይገባል፡፡ ሁለተኛው ሁኔታ በፌዴራል መንግሥቱና በክልሎች መካከል ግጭት ወይም አለመግባባት በሚኖርበት ጊዜ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ የሚያስታርቅ አካል መኖር አለበት፡፡ ይኼ አካል የፍርድ ቤቶች ባህርያት ሊኖሩት ይገባል፡፡ እኔ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፖለቲካ ተቋም ስለሆነ ሕገ መንግሥቱን ሊተረጉም አይገባም የሚለውን ክርክር አልደግፍም፡፡ ሕገ መንግሥት የሕግ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ሰነድም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚወክለው ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ቢሆንም፣ በተግባር የሚያንሸራሽረው የክልሎችን አቋም ነው የሚለውን ክርክር እንዴት ያዩታል? በድምፅ ደረጃስ ብዙ ሕዝብና ብሔሮች ያሏቸው ክልሎች በርካታ አባላት እንዲኖራቸው መደረጉን እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር አበራ፡- ብዙ ብሔሮች ያላቸው ክልሎች በምክር ቤቱ የተሻለ ድምፅ አላቸው፡፡ እነዚህ በአንድ ክልል የሚገኙ ብሔሮች ተመሳሳይ አቋም ሊያንፀባርቁ ይችላሉ፡፡ ደቡብ ክልል በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስላሉት በርካታ ተወካዮች በምክር ቤቱ አሉት፡፡ የኦሮሚያና የአማራ ክልል ተወካዮች ተደምረው ከደቡብ ያንሳሉ፡፡ ይኼ ውሳኔ አሰጣጡን ዴሞክራሲያዊ አያደርገውም፡፡ ይኼ ክልሎችን መወከል ለምን ብሔሮችን በመወከል ተቀየረ የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡

ሪፖርተር፡- በተግባር ደረጃ የፌደራልና የክልል አስፈጻሚ አካል አባላት የሆኑ ሰዎች የክልል ፕሬዚዳንቶችን ጨምሮ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል ሲሆኑ ይታያል፡፡ ይኼ በራስ ጉዳይ ላይ ዳኛ መሆን አይቻልም ከሚለው መርህ ጋር አይጋጭም?

ዶ/ር አበራ፡- የፖለቲካ ትኩሳት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ምክር ቤቱ የመሸሽ አዝማሚያ ያሳያል፡፡ እስካሁን ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጭ ነው ብሎ ውሳኔ የሰጠው በአቶ መላኩ ፈንታ የይግባኝ መብት ላይ ብቻ ነው፡፡ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔውም በተመሳሳይ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ጠልቆ አይገባም፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትንና የአስፈጻሚውን አካል ውሳኔ ተገዳድሮ አያውቅም፡፡ ይኼ ዞሮ ዞሮ ከፖለቲካ ምኅዳሩ ጋር ይገናኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር ለመደበኛ ፍርድ ቤቶች ከተሰጠው የዳኝነት ሥልጣን አንፃር ልዩነቱ በውል የተለየ አይደለም ተብሎ የሚቀርበውን ክርክር እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር አበራ፡- ፍርድ ቤቶች ወይም የዳኝነት አካላት ራሳቸው ሥልጣናቸውን የሚያስከብሩ አይደሉም፡፡ እንኳን ተፈጥሯዊ ሥልጠናቸውን በመጠቀም ሊሟገቱ በግልጽ የተሰጠ ሥልጠናቸውንም የሚጠቀሙ አይመስሉም፡፡ በተለይ ጉዳዩ የፖለቲካ ትኩሳት ያለው በሚሆንበት ጊዜ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መምራትን ይመርጣሉ፡፡ ምክር ቤቱም ጉዳዮችን በአግባቡ የመመርመርና ውሳኔን በተቀላጠፈ ሁኔታ የመስጠት ሪኮርዱ ደካማ ነው፡፡ ሁለቱም ፍርኃት አለባቸው፡፡ በመሀል እየተጎዳ ያለው ጉዳዩ ውሳኔ እንዲያገኝ የሚጠይቀው ዜጋ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የሚነሱ በርካታ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች ቢኖሩም፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ወይም ለአማካሪው የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ እስካሁን የቀረቡት በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ይህ አንዳንዶች ሕገ መንግሥቱ ገና ያልተፈተነ ነው እንዲሉ አድርጓቸዋል፡፡ እርስዎ በዚህ ይስማማሉ?

ዶ/ር አበራ፡- በቡድኖችም ሆነ በግለሰቦች ከሕገ መንግሥቱ ጋር የተገናኙ ቅሬታዎች ይኖራሉ፡፡ ለአንዳንዶች የማንነት ጥያቄ ይሆናል፡፡ ለሌሎች ደግሞ አዲስ የወጣው አዋጅ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን መብት ነክቶ ሊሆን ይችላል፡፡ በምታነሳው ጥያቄ ሌላ ተጨማሪ ጉዳት ይደርስብኛል ብለህ ከሰጋህ ጥያቄ ለማቅረብና ሥርዓቱን ለመፈተን አትበረታታም፡፡ አንዳንድ ጉዳዮችም ከሕጋዊ መንገድ ይልቅ በፖለቲካ ሲፈቱ ነው የሚታየው፡፡ ነገር ግን መፍትሔው ሁሉንም የሚያስማማ ከሆነ ሁሉም ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ወይም ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መሄድ አለበት ብዬ አላምንም፡፡ አስቀድሞ በሥራ ላይ የነበረው ሥርዓት ውጤታማ ሆኖ አዲሱ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንግዳ የሆነበት ሕዝብ ይኼኛውን መንገድ ውድቅ ሊያደርግ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ላይ ምርምር የሚሠሩ ምሁራን በርካታ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ይጠይቃሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያን የመፍራት አዝማሚያ አለው ተብሎ ይተቻል፡፡ ይህን ተቃርኖ እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር አበራ፡- ሕገ መንግሥት በመርህ ደረጃ የሕዝብ ነው፡፡ ሕዝቡ የባለቤትነት ስሜት ሊኖረው ይገባል፡፡ ስለዚህ ከሕገ መንግሥታዊ ቅቡልነት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ካየነው ማንኛውም አካል ይኼ ሕገ መንግሥት ሊሻሻል አይገባም ሊል አይችልም፡፡ ማሻሻያ ጥያቄው ሕዝባዊ ድጋፍ ካለው ማንም በር ሊዘጋ አይችልም፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ የሚጠየቅባቸው ጉዳዮች በአብዛኛው በማርቀቅ ሒደቱ ጊዜም አወዛጋቢ የነበሩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ የመሬት ባለቤትነትና የመገንጠል መብትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ያኔ በድምፅ ብልጫ የተሸነፉ አካላት በጊዜ ሒደት አብላጫ ድምፅ ሊኖራቸው ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች በእኩልነትና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ከዚች አገር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሕገ መንግሥቱ ምን ዓይነት ሚና ተጫውቷል?

ዶ/ር አበራ፡- ተጠቃሚነትን የምንለካው በምንድን ነው? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ ተሳትፎና ተደራሽነት ይኼን ለመለካት ወሳኝ ነገሮች ናቸው፡፡ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለሁሉም ተደራሽ መሆን አለበት፡፡ አሁን ሁሉም እኩል ተጠቃሚ ነኝ ብሎ ይገምታል ወይ ብለህ መጠየቅ አለብህ፡፡ መሬት ከደሃው ይልቅ ሀብት ላለው ዜጋ ነው ተደራሽ እየሆነ ያለው፡፡ በኢትዮጵያ እየመጣ ያለው ልማት ማንን ነው ተጠቃሚ እያደረገ ያለው የሚለውም ጥያቄ መልስ የሚያሻው ነው፡፡ በቅርቡ ከተደረገው ምርጫ አንፃር የፖለቲካ ምኅዳሩ ጠቧል ሳይሆን ተዘግቷል የሚሉ እየተበራከቱ ነው፡፡ የፖለቲካ ሥልጣን ለሁሉም ተደራሽ መሆኑ ላይ የምርጫው ውጤት ጥርጣሬ ያስነሳል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ግን ቃል የገባው ይህን ዓይነት ሥርዓት ለመፍጠር አይደለም፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት፣ የመደራጀት መብት፣ ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት መብት፣ ፍትሐዊ ውክልናን የሚያረጋግጥ ሕገ መንግሥት በተግባር ላይ ውሏል ወይ ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ጥርጣሬ ቢኖረኝም ሕዝቡ እንዲህ ነው የሚያስበው ብዬ ልናገር አልችልም፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ገዥው ፓርቲ የሚከተለው የልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ጋር የሚስማማ አይደለም በሚል የሚተቹ አሉ፡፡ የእርስዎ አቋም ምንድን ነው?

ዶ/ር አበራ፡- ሕገ መንግሥቱ በመሠረቱ የሊበራል አስተሳሰብ የሚያራምድ ነው፡፡ የሚያበረታታው የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓት ከታች ወደ ላይ የሚሄድ ነው፡፡ የሕዝብን ፍላጎት መሠረት አድርጎ የሚሄድ የውሳኔ አሰጣጥ ነው የዘረጋው፡፡ ልማታዊ መንግሥት ይኼን አሠራር የሚገለብጥና ከላይ ወደ ታች የሚወርድ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ የአውራ ፓርቲ ሥርዓት ቦታ የለውም፡፡ ይኼ ሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡ በርካታ መርሆዎችን አላስፈላጊ የሚያደርግ ሥርዓት ነው፡፡ በኢሕዲሪ ሕገ መንግሥት ላይ የተቀመጠ ሥርዓት ነው፡፡ ልማታዊ መንግሥት በኢትዮጵያ ያሉትን እንደ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ የፖለቲከ አመለካከትና መሰል ብዝኃዊነትን ለማስተናገድ የሚያስችል አይደለም፡፡ አንድ ወጥ አመለካከት በዚህች አገር ተረጋግጧል ማለት የሚያሳምን አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ካለው የድህነት ሥር መስደድ አኳያ ያሉትን የተለያዩ ልዩነቶች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማስተናገድ መሞከር ከድህነት በፍጥነት ለመውጣት አያስችልም በሚል የሚቀርበውን ክርክር እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር አበራ፡- ዴሞክራሲ የጋራ ራዕይ ላይ ያተኮረ አስተዳደር ይዘረጋል፡፡ የተለያዩ አመለካከቶችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ካስተናገድን ልማትን በፍጥነት አናመጣም ለሚሉ አካላት የማቀርብላቸው ጥያቄ ስለማን ልማት ነው የምታወሩት ነው፡፡ ስለ ሕዝቡ ልማት የሚያወሩ ከሆነ ይኼ አመለካከት ስህተት እንደሆነ ይረዳሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብን ያልተመለከተ ልማትን እኔ ልማት ልለው አልችልም፡፡ አንድ ፓርቲ ሕዝቡ ላይ የሚጭነውና ሌላው አብዛኛው ዜጋ የማይጋራው፣ የተለዩ አመለካከቶችን የማያስተናግድ ልማትን ልማት ልለው አልችልም፡፡ አንድ ቡድን ስለልማት ያለውን አረዳድ ሌላው ላይ መጫን አለበት ብዬ አላምንም፡፡ ልማት መብት ተኮር መሆን አለበት፡፡ ሰው ሰው የሚሸትና ሰብዓዊነት ገጽታ የተላበሰ ልማት ነው ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት፡፡

ሪፖርተር፡- ሕገ መንግሥቱ ባለፉት 20 ዓመታት ከሄደበት ጉዞ የተሻለ በመጪዎቹ 20 ዓመታት እንዲጓዝ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ዶ/ር አበራ፡- ለሁሉም ክፍት የሆነ የፖለቲካ ከባቢ ሁኔታን መፍጠር ዋናው ተግባር መሆን አለበት፡፡ ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ተግባራዊ መሆን አለበት፡፡ እያንዳንዱ ቡድንና ዜጋ የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ የመወስን ዕድል እንዳለው ሊያምን ይገባል፡፡ ይህ ካልተፈጠረ የሕገ መንግሥቱ ቀጣይነትም ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ ካልሆነ ይህም ሕገ መንግሥት ዕጣ ፈንታው ከዚህ በፊት እንደነበሩት ይሆናል፡፡ ይኼ አካል ዕድል ካገኘ ይኼኛውን አንቀጽ ይቀይራል የሚለው ነገር አያዋጣም፡፡ የሕዝቡ ፈቃድ ከሆነ ሊከለከል አይገባም፡፡ አግላይ የሆነ ሥርዓት ይዞ መቀጠል አደጋ አለው፡፡
ምንጭ ራፖርተር


Viewing all articles
Browse latest Browse all 3774

Trending Articles