የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን /ካፍ/ የቶጎ ብሔራዊ ቡድን ከ2017 የአፍረካ እግር ኳስ ዋንጫ የማጣሪያ ውድድር በራሱ ጥያቄ በመውጣቱ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን በዝርክርክ የፌዴሬሽኑ አሰራር ሊያጣው ወደቻለው ውድድር እንዲመለስ አደረገ።
በወጣው የካፍ ድልድል መሰረት የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን /ሉሲዎቹ/ ከአልጄሪያ አቻው ጋር ከየካቲት እስከ መጋቢው ወር ባለው ጊዜ ውሰጥ የሚያደርጉ ሲሆን የመጀመሪያው ጨዋታ በአልጀርስ የሚከናወን ሲሆን፥ የመልሱ ደግሞ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጿል።
የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ምዝገባ በተመለከተ ካፍ ሦስት ጊዜ ለጻፈው ደብዳቤ ምላሽ ባለመስጠቱ ሉሲዎቹ ከአፍሪካ ዋንጫ ውጪ መሆናቸው የሚታወስ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ዛሬ ባወጣው መግለጫ “የሉሲዎቹ ተሳትፎ እንዲቀጥል ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት በተለይም የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት በካይሮ የካፍ ዋና ጽህፈት ቤት እንዲሁም በርዋንዳ ኪጋሊ የቻን ውድድር ወቅት ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የካፍ የስራ ሃላፊዎችን በማነጋጋር ያከናወኑት ዲፕሎማሲያዊ ተግባር የሚፈለገውን ውጤት አስገኝቷል ” በማለት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሉሲዎች ወደውድድሩ መመለስ በጥረት ያገኘሁት ነው የሚል መግለጫ አውጥቷል፡፡
የስፖርት ባለሞያዎች የቶጎ ብሔራዊ ቡድን ከ2017 የአፍረካ እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ መውጣቱ የሰጠንን እድል የፌዴሬሽኑን ድክመት ለመደበቂያ መጠቀም ያሳፍራል ይላሉ።