• በመላው ዓለም እየዞሩ በመስራት ከ5 ሚ. ብር በላይ አጠራቅመው ነበር
• እሳቸውና ባለቤታቸው በመታመማቸው ገንዘቡ በህክምና አለቀ
• አሁን ገቢያቸው ከቤት ኪራይና ከጡረታ 1500 ብር ገደማ ነው
• “ህዝቡ ሲፈልግ ያሳክመኝ፤ ያለበለዚያ ስሞት ይቅበረኝ”
ጌታቸው መኩሪያ በሳክስፎን ተጫዋችነቱ አንቱ የተባለ አንጋፋ ባለሙያ ነው፡፡ በማዘጋጃ ቤት፣ በብሄራዊ ቴአትርና በፖሊስ ሰራዊት የሙዚቃ ክፍል ከሙዚቃ ተጫዋችነት እስከ ዋና መምህርነት አገልግሏል፡፡በ1986 ዓ.ም ጡረታ ከወጣ በኋላ በሸራተን አዲስ ሆቴል ለስምንት አመታት የሰራው አንጋፋው ሙዚቀኛ፤ ከመቶ በላይ አገራትን በሥራ አጋጣሚ ዞሯል፡፡ አልቶ ክላርኔት እና ሳክስፎን አሳምሮ የሚጫወተው አርቲስቱ፤ ከሦስት አመታት ወዲህ በህመም ምክንያት ከሚወደው ስራው ርቆ የበርካታ ሆስፒታሎችን ደጃፍ ለመርገጥ ተገድዷል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከ81 ዓመቱ የእድሜ ባለፀጋ ከጌታቸው መኩሪያ ጋር በጤናው፣ በሙያውና በአጠቃላይ ህይወቱ ዙሪያ ሰፊ ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡
የጤና እክል እንዳጋጠመህ ሰምቻለሁ፤ ህመምህ ምንድን ነው?
የልብ ችግር ቀደም ሲል ነበረብኝ፡፡ አሁንም ያው የልቤ ህመም ነው የተባባሰብኝ፡፡ በዚያ ላይ ሁለቱም እግሬ ታፋዬ ላይ አብጦ መራመድ አልቻልኩም፤ ብቻ ተደራርቦብኛል፡፡
ህክምና አላገኘህም እንዴ?
ፖሊስ ሆስፒታል በነፃ መታከም እችላለሁ፤ ግን እዛ ለበሽታዬ መፍትሄ አልተገኘም፤ ላንድማርክም ታክሜያለሁ፤ ውጤት አላገኘሁም፡፡ አሁን ይሄው ኮሪያ ሆስፒታል ዛሬ ሄጄ (ቃለ ምልልሱ ረቡዕ ነው የተደረገው) ውጤት ዘጠኝ ሰዓት ብለውኛል፡፡ እስኪ የሚሆነውን አያለሁ፡፡ እዚህ ካልተቻለ ታይላንድ ባንኮክ ሄደህ ትታከማለህ እያሉኝ ነው፡፡ እግዚአብሄር ያውቃል፡፡
አሁን ሙሉ በሙሉ መራመድ አትችልም?
አልችልም፡፡ በሰው ድጋፍ በምርኩዝ በስንት ችግር ነው የምንቀሳቀሰው፡፡
ስለዚህ ስራ እየሰራህ አይደለማ?
እንዴት አድርጌ… እግሬ አላላውስ ብሎኛል፡፡
በሙዚቃ ህይወት ምን ያህል ጊዜ አሳለፍክ?
ከ60 ዓመታት በላይ ቆይቻለሁ፡፡ በ1940 ዓ.ም ወዳጄነው ፍልፍሉ የሚባል ጓደኛዬና ተፈራ አቡነወልድን አይቼ ነው ወደ ሙዚቃው የገባሁት፡፡ ወዳጄነው ፍልፍሉ ጐበዝ ክላርኔት ተጫዋች ነበር፡፡ ተፈራም ከማዘጋጃ እስከ ብሄራዊ ቴአትርና እስከ ውጭው ዓለም ድረስ ብዙ ታሪክ የሰራ፣ ድንቅ የጥበብ ሰው ነበር፡፡ አሁን ሁለቱም በህይወት የሉም፡፡ መጀመሪያውኑ ዋሽንት መጫወት፣ ሰርግ ላይ መጨፈር እወድ ነበር፡፡ እነተፈራን ሳይ ደግሞ ፍላጐቴ ጨመረና ማዘጋጀ ቤት ገባሁ፡፡ ከዚያ ትንሽ ሰልጥኜ የመንገድ ላይ ታምቡር (ድራም) አስያዙኝ፤ በኋላ እራሴን እያሻሻልኩ ወደ ክላርኔት ተሸጋገርኩ፡፡ ከክላርኔት ወደ ሳክስፎን አሻሻልኩ ማለት ነው፡፡
እዚያው ማዘጋጃ ቤት ተቀጠርክ ማለት ነው?
አዎ! ማዘጋጃ ቤት ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻልኩ ስመጣ፣ ደሞዝ የሁለት የሁለት ብር ጭማሪ ሲደረግ፣ ስንወዳደር ሁሉንም በልጬ ተቀጠርኩኝ፡፡ እነዚያ የበለጥኳቸው ልጆች ተናደው መንገድ ላይ ጠብቀው ደበደቡኝ (ረጅም ሳቅ…)
በጣም ተጐዳህ?
ድብደባው እንኳን እስከዚህም ነው፤ እንደው ነገሩ ነው እንጂ፡፡
የመጀመሪያው ቅጥር ደሞዙ ስንት ቢሆን ነው የሁለት ብር ጭማሪ የተደረገው?
(በጣም እየሳቀ)… ደሞዙማ አስር ብር ነበር፤ መጀመሪያ ስቀጠር፡፡ በውድድሩ እነሱን በልጬ 18 ብር ስለገባሁ አይደለም እንዴ ባልደረቦቼ ደበደቡኝ ያልኩሽ፡፡
ከዚያስ?
ከዚያማ እንዲህ እንዲህ እያልን… በሶስተኛው ዓመት በ1943 ዓ.ም መሆኑ ነው፡፡ ኮሪያ ዝመቱ ተባልን፡፡ በወቅቱ መንግስቱ ነዋይ ኮሎኔል ነበር፤ መጣና፤ “ይህችን ልጅ ተዋት፤ ጥይት አታባክኑ” ብሎ ነገራቸው፡፡ ተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ) ሲዘምት፣ እኔ ቀርቼ በሙዚቃው ቀጠልኩ፡፡ ከተስፋዬ ጋር ሌሎችም ዘምተዋል፡፡ ምክንያቱም እኔ ያን ጊዜ ቀልጣፋና ጐበዝ ነበርኩ፡፡ እነሱ ሰነፍ ስለሆኑ ዘመቱ ማለቴ ግን አይደለም፡፡
ለመሆኑ የሙዚቃ መሳሪያዎቹን ማን አሰለጠነህ?
እኔ ቀደም ብዬ ስትተዋወቂኝ እንዳጫወትኩሽ፣ ሳልማር ያስተማርኩ ነኝ ብዬሻለሁ፡፡ በቀለም ትምህርት እስከ ዘጠነኛ ክፍል ነው የተማርኩት፣ ከዚያ በላይ አልገፋሁም፡፡ የሙዚቃ መሳሪያዎቹን ያስተማሩኝ ግን ነርሲስ ናልቫንዲያን እና ዘልቤከር የተባሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ከዚያ እራሴን እያሻሻልኩ በመሄዴ፣ የነርሲስ ረዳት ሆኜ በመምህርነት በርካታ ሰዎችን አስተምሬያለሁ፡፡
በወቅቱ ደራራ ባይሳ የተባለ በኋላ ስሙን ቀይሮ ተድላ ተብሏል፤ እሱ ጐበዝ ሳክስ ተጫዋች ነበር፤ ሁለተኛ እኔ ነበርኩኝ፤ በጥረቴ አንደኛ ሆኜ ረዳት መምህር ሆንኩኝ፡፡
ከማዘጋጃ ቤት በ1948 ወደ ብሄራዊ ቴአትር ቤት ተዛወርክና በርከት ላሉ አመታት እዚያ ሰራህ፣ ከዚያም ወደ ፖሊስ ሙዚቃ ክፍል ገባህ፡፡ እስኪ ሂደቱን አስታውሰኝ?
ልክ ነው በ1948 ብሄራዊ ቴአትር ከገባሁ በኋላ ለ17 አመታት ሰርቻለሁ፡፡ ጥሩ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት፡፡ ከዚያ ወደ ፖሊስ የተዛወርኩት የነርሲስ ረዳት መምህር ሆኜ ነው፤ መቼም ፖሊስ ውስጥ እኔና ሂሩት በቀለ ከሌለን ቤቱ አይደምቅም ነበር፡፡ እኔና እሷ ፖሊስን ፖሊስ አሰኝተነው ነው ያለፍነው፡፡ ለበርካታ አመታት አስተማሪም ተጫዋችም ሆኜ ጡረታ እስከወጣሁበት ጊዜ ድረስ አገልግያለሁ፡፡
በ1986 ዓ.ም ነው ጡረታ የወጣኸው አይደለም?
ልክ ነው ከመንግስት ለውጥ ከሦስት አመት በኋላ ነው ጡረታ የወጣሁት፡፡
ፖሊስ ሙዚቃ ክፍል ምክትል መምህር ሆነህ ስትሰራ ዋናው መምህር ነርሲስ ናልቫንዲያን በመሞታቸው፣ ዋና መምህር ሆነህ ነበር፡፡ ለመሆኑ የ18 ብር ደሞዝህ ስንት ደረሰ?
ነርሲስ ሲሞት እኔ ዋና መምህር ሆንኩኝ፡፡ ደሞዙ 800 ብር ነበር፡፡ የእሱ ደሞዝ እንዲከፈለኝ ከተደረገ በኋላ ተስፋዬ አበበ አብሮ ለፍቷል፤ በጀት ውስጥ ይግባ ተባለና የኔ ደሞዝ ለሁለት ተከፍሎ፣ እኔ 600 ብር ሆነ ደሞዜ፡፡
ዶ/ር አርቲስት ተስፋዬ አበበ ናቸው?
አዎ፡፡ እሱንም እንደኔ ረስተውት ነበር፡፡ አሁን አስታውሰው ዶ/ር አድርገውታል፤ እውነት ለመናገር ይገባዋል፡፡ ዘግይተውም ቢሆን ይህን ክብር ስለሰጡት ደስ ብሎኛል፡፡
ጡረታ ከወጣህ በኋላ ሸራተን መስራት እንደጀመርክ ይታወቃል፡፡ ከዚያም ከመቶ በላይ የዓለም አገራትን በስራ መዞርህንም አውቃለሁ፡፡ እስኪ ስለሱ አጫውተኝ?
ልክ ነው ሸራተን ገብቼ ስጫወት የፈረንጅ መአት ይመጣ ነበር፡፡ እኔ እንደነገርኩሽ ብዙ ቋንቋ አልችልም፤ በማህሙድ አህሙድ አስተርጓሚነት ከፈረንጆቹ ጋር ተነጋገርኩና ውጭ መሄድ ጀመርኩ፡፡ ብቻ ምን አለፋሽ… ወደ 104 አገራትን አይቻለሁ፡፡ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ሆላንድ፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ… ከመላኩ በላይ ጋር እየዞርን፣ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ አሰኝተናታል፡፡ አሜሪካ እንኳን ሰባት ስቴት ውስጥ ስራዬን አቅርቤያለሁ፡፡ እስራኤልም እንዲሁ… ብቻ አሁን የማስታወስ ችሎታዬ ቀንሷል… ድፍን አለምን ዞሬያለሁ፡፡
የማስታወስ ችሎታዬ ቀንሷል ስትል… ለእርጅና እጅ ልትሰጥ ነው እንዴ?
ኧረ የለም አልሰጥም፤ ገና የ81 አመት አፍላ ጐረምሳ እኮ ነኝ፡፡ በ1927 እኮ ነው የተወለድኩት፡፡
ክፍለሀገር ነው የተወለድከው?
አዎ፡፡ ይፋትና ጥሙጋ ነው፡፡ ልጅ ሆኜ ነው አዲስ አበባ የመጣሁት፤ እስከ ዘጠኝ ተምሬ እንደነገርኩሽ ወደ ሙዚቃው ገባሁ፡፡
ከ100 በላይ የአለም አገራትን ስትዞር መቼም ጥሪት መቋጠርህ አይቀርም ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን ያገኘሁህ ግን በሰዎች እርዳታ ስትታከም ነው፡፡ አሁን ምንም ንብረት የለህም ማለት ነው?
እንዳልሽው ጥሪት ቋጥሬ ነበር፡፡ ለልጆቼም ለጥቂቶቹ ላዳም ገዝቼ ሰጥቼ ነበር፡፡ መለስተኛ ቤትም አለኝ፡፡ ነገር ግን ባለቤቴም እኔም ታመን ያልሄድንበት ሆስፒታል፣ ያልታከምንበት ሀኪም ቤት የለም፡፡ ግን ገንዘቤን አሟጥጬ ከመጨረስ በቀር መፍትሄ አላገኘሁም፤ በመጨረሻ ከስድስት ወር በፊት ባለቤቴ አረፈች፡፡ (በጣም ትካዜ ውስጥ ገባ) ገንዘቤ ሲያልቅ መልሼ ፖሊስ ሆስፒታል አስገብቻት ነበር፡፡ የልብ ህመም ነበረባት፤ አልዳነችም፡፡ ምን አለፋሽ… ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ አጠራቅሜ ነበር፤ አሁን ይሄው መላኩ ነው እየደገፈኝ ያለው፡፡
ብዙ ልጆች እንዳሉህ ሰምቻለሁ፤ አይረዱህም?
ዘጠኝ አካባቢ ልጆች አሉኝ፤ የቁጥራቸው መብዛት ፋይዳ የለውም፡፡ በአጭሩ ለራሳቸውም በቂ ኑሮ እየኖሩ አይደለም፡፡
ከሸራተን ስራ ያቆምከው ለምን ነበር?
ሸራተን እየሰራሁ እንዳልኩሽ ለስራ ብዙ ጊዜ ወደ ውጭ እወጣ ነበር፡፡ “እዚህ እየሰራህ እንዴት ውጭ ሄደህ አንድና ሁለት ወር እየቆየህ ትመጣለህ?” አሉኝ፡፡ ታዲያ ስራ ላልሰራ ነው፤ ከፈለጋችሁ ተውት እንጂ ውጭ መሄዴን አላቆምም ስል፣ ለሼህ አላሙዲን ነገሩት እና አቀያየሙን፡፡ እንደውም እሱ የገዛልኝን ሳክስፎን እንመልስልሃለን ብለው ወስደው ሸጡት፡፡
እነማን ናቸው የሸጡት?
የኔ ልጅ ተይው እከሌ ነው እከሌ ነው ማለቱ ጥቅም የለውም፡፡ ስም ለመጥራትም ያስቸግራል፡፡ ብቻ ያልኩሽ ሆኗል፡፡ እኔም በጣም ተቀየምኩኝ፡፡
እና አሁን ሳክስፎን የለህም?
ኧረ ደንበኛው ሳክስፎን ነው ያለኝ፡፡ ክላርኔትም አልቶም አለኝ ሶስትና አራት መሳሪያ ነው የምጫወተው፡፡ ይሄው ሶስት አመት ስታመም ተረስቼ ቀረሁ፤ ጤናው ቸገረኝ እንጂ መሳሪያው አለኝ፡፡ አሁን ለብሄራዊ ቴአትር 60ኛ አመት በዓል እኔና መርአዊ ስጦት በተቻለን መጠን አንድ ሙዚቃ ለመጫወት አስበናል፤ ከተሻለኝ ማለቴ ነው፡፡ ያው እሱም ልቡን ያመዋል እንደሚታወቀው፡፡
አሁን ከማን ጋር ነው የምትኖረው? ማንስ ነው የሚጦርህ?
አንድ ሴት ልጅ አለችኝ፡፡ እሷ ብቅ እያለች ታየኛለች፤ በቃ ከሰራተኛ ጋር ነው የምኖረው፡፡
የገቢ ምንጭህ ምንድነው?
ቤት አለኝ ብየሽ የለም፤ ሁለት ትንንሽ ክፍሎች አከራያለሁ፤ ከእነሱ ወደ አንድ ሺህ ብር አካባቢ አገኛለሁ፡፡ ጡረታዬ አሁን በጭማሪው ሁለት መቶ ብር ተጨምሮልኝ ወደ አምስት መቶ ከፍ ብሏል፤ እሷን እሷን እያደረግሁ ነው የምኖረው፡፡
ለህክምና ባንኮክ ያልከውስ…?
እንኳን ባንኮክ ሄጄ የምታከምበት አሁን ሃኪም ቤት የምመላለስበትንና የምታከምበትን እንኳን የሚከፍልልኝ ይሄው መላኩ በላይ ነው፡፡ እንግዲህ ፈጣሪ ያውቃል፡፡
ብዙዎቹ የአገር ባለውለታዎች በህመምና በገንዘብ ማጣት ሲቸገሩ ብዙ አያገኙም፤ “ሲሞቱ ግን ቀብራቸው ይደምቃል” ይባላል፡፡
ልክ ነው፡፡ እኔ አንድ የምወደው አባባል አለኝ፤ “ከሞተ ጀነራል የቆመ ወታደር ይሻላል” የሞተን ሰው ጀነራል ከማድረግ፣ ለቆመው ወታደር እንክብካቤ መስጠት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ጀነራል፣ ሚኒስትር፣ ደጃዝማች እያሉ ማሞካሸትና መካብ የወሬ ጋጋታ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ያን ያህል ክብር ከሰጡት በቁም የሚያስፈልገውን እንክብካቤ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ እኔም አሁን ታምሜ ብረሳም ሲሻለኝ ብቅ ብዬ ህዝቡን አለሁ እለዋለሁ፡፡ ህዝቡ ራሱ እንደሚያሳክመኝ አምናለሁ፡፡ እዚያ ከመድረሴ በፊት ግን ሁሉም በየእምነቱ እሱ እንዲምረኝ ይፀልይልኝ፡፡
እስኪ ማዘጋጃም ብሄራዊ ቴአትርም ፖሊስ ክበብም ስትሰራ ያጋጠመህና የማትረሳቸው ፈገግ የሚያሰኙ፣ የሚያሳዝኑ ገጠመኞች ካሉህ አጫውተኝ…
አንዱ ቀደም ብዬ የነገርኩሽ ነው፡፡ ማዘጋጃ ቤት ተወዳድረን ሳሸንፋቸውና ደሞዜ 18 ብር ሲገባ ባልደረቦቼ የደበደቡኝን አልረሳውም፡፡ እንደውም ሳስታውሰው ያስቀኛል፡፡ ሌላው ፖሊስ ሙዚቃ ክፍል ውስጥ እያለሁ የሚሊታሪ ልብስ እለብስ ነበር፤ ቅጥሬ ግን በሲቪል ነው፡፡ የሚሊታሪውን ልብስ ስለብስ ግን ከጀነራሉ የበለጠ ያምርብኛል፡፡ ሲያዩ የማእረግ ምልክት የለውም፤ ምንድነው ማእረግህ፤ “ኮሌኔል ባሻ” እላለሁ፡፡ ሌላውም ሲጠይቀኝ፤ “ኮሎኔል ባሻ” እላለሁ፡፡ ይሄ በሰራዊቱ ውስጥ የሌለ ማእረግ ነው፤ ግን እነሱ ይኑር አይኑር አያውቁትም፡፡
ይሄን የምለው ናቅፋ አልጌና እና አውራሮ ስሄድ ነው፡፡ ሌላ ጊዜ ሲጠይቁኝ፤ “አሁንማ ጀነራል ባሻ ሆኛለሁ” ስል አንድ ችኩል የሆነ ኮሎኔል አያሌው አበበ የሚባል አለቃ ነበረኝ፤ “ዝም በሉት፤ እንዲህ የሚባል ማእረግ የለም፤ እሱ ሲቪል ነው” ብሎ አዋረደኝ እልሻለሁ (ረጅም ሳቅ…)
ታዲያ ያኔ ጦር ሰራዊቱ አዲስ ማእረግ የመጣ እየመሰለው፤ “ጀነራል ባሻ” እያለ ወታደራዊ ሰላምታ ገጭ ያደርግልኛል፡፡ እኔም ምላሹን እሰጥ ነበር፡፡
አንዴ ደግሞ ሱዳን ሄጄ ሙቀቱ ሲያስቸግረኝ ሻወር ለመውሰድ ገንዳውን ውሃ ከፍቼ እየሞላሁ፣ እዚያው ባለሁበት እንቅልፍ ጭልጥ አድርጐ ወሰደኝ፡፡ ውሃው ከገንዳው አልፎ እስከ ውጭ ድረስ ይፈሳል ለካ፡፡ ሰራተኞቹ እንደምንም በመስታወት ተንጠራርተው ሲመለከቱ፣ ውሃው ውስጥ ተኝቻለሁ፡፡ “ወፍራም ሰው ገንዳ ውስጥ ሞቷል” ብለው መጮህ ጀመሩ፡፡ ከዚያ በሩን በሃይል ክፍት ሲያደርጉት፣ ብንን ብዬ ተነሳሁ፡፡ “አስደነገጥከን እኮ” ብለው ጮሁ፤ ይሄ ብሄራዊ ቴአትር ስሰራ ሱዳን ሄጄ ነው የተከሰተው፡፡
አሁን ከድሮ ጓደኞችህ ጋር ትገግኛለህ… ትጠያየቃለህ?
አዎ ከድሮ ጓደኞቼ ጋር አልፎ አልፎ እንጠያየቃለን፤ በተለይ ከመርአዊ ስጦት ጋር፡፡ ከግርማ፣ ከተስፋዬ አበበ፣ ከአፈወርቅ ጋር እንገናኛለን፡፡ ማህበርም አለን፤ በብሄራዊ ቴአትር በኩል፡፡ በግልም የሽማግሌዎች ማህበር አለን፡፡ እኔ ስላመመኝ ነው እንጂ በየወሩ ቅዳሜ ቅዳሜ እንገናኝ ነበር፡፡
በወጣትነትህ ምን አይነት ባህሪ ነበረህ? ለመጀመሪያ ጊዜ ትዳር የመሰረትከው በቅርብ ካረፉት ባለቤትህ ነው ወይስ?
እኔ በወጣትነቴ ሌላ ሚስት ነበረችኝ፡፡ የመጀመሪያው ትዳሬ ጥሩ አልነበረም፡፡ አሁን በቅርብ ካረፈችው ባለቤቴ ጋር ከተጋባን 55 አመታችን ነው፡፡ ከመጀመሪያው ትዳሬ ሦስቱ ልጆች ቢወለዱም አብዛኛዎቹ ከዚህችኛዋ የተወለዱ ናቸው፡፡ የጨዋ ቤተሰብ ልጅና መልካም ሴት ነበረች፤ መልክና ቁመናዋም ሌላ የሚያሳይ አልነበረም፡፡ ከሷ በኋላ ወደዚህም ወደዚያም ሳልል፣ በሰላምና በፍቅር ነው የኖርነው፤ ሞት ለያየን እንጂ፡፡ ብቻ ነፍሷን ይማረው፡፡በኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት፣ በደርግ አሁንም በኢህአዴግ … በሦስት መንግሥታት ኖረሃል፡፡ በእነዚህ ሦስት መንግስታት የሙዚቃ ሁኔታ… አጠቃላይ የስርአቶቹ ሂደት በአንተ አስተያየት ምን ይመስላል?
እኔ እንግዲህ ሽማግሌ እንደመሆኔ የአድርባይነት ወሬ አላወራሽም፡፡
ይህችን አገር በስልጣኔውም ሆነ በሁሉ ነገር መሰረት ያስያዟት አፄ ምኒልክ እና ኃይለስላሴ ናቸው፡፡ በኋላ መንግስቱ ኃይለማሪያም የሚባል አገር አጥፊ መጥቶ፣ አገሪቱን እንዳልነበረች አደረጋት፡፡ አሁን ብዙ ሰው “መንግስቱ የሀገር ፍቅር አለው” ብሎ ይከራከራል፤ አገሩን የሚወድ ሰው ያንን ሁሉ የአገሪቱን ምሁራን ሰብስቦ ይጨርሳል እንዴ? እሱ የሚወደው ራሱንና ስልጣኑን ነበር፡፡ ከዚያ አገር አጥፊ መቼም አንደኛውን ኢህአዴግ ይሻላል፡፡ እንግዲህ ኢህአዴግንም ሆነ ደርግን ብወድም ባልወድም መብቴ ነው ግን ኢህአዴግንም የምነቅፍበት ብዙ ጐኖች አሉኝ፡፡
ለምሳሌ?
ለምሳሌ ኤርትራን አስገንጥሎ አገሪቱን የባህር በር በማሳጣቱ፣ አንቀፅ 39ን አምጥቶ ህዝብ በመከፋፈሉ ቅር እሰኛለሁ፡፡ ከተማዋም ብትሆን በእቅድ ብትገነባ ጥሩ ነው፤ ህዝቡ አሁን በመቶ ብር አንድ ፌስታል እቃ አይሸምትም፤ ነፃ ገበያ እየተባለ ማንም የሚፈነጭባት አገር ሆናለች፡፡ ይሄ ይሄ ቢስተካከል ኢህአዴግ ጥሩ ይሆን ነበር፡፡
ምህረቱን ይስጥህ… ጋሽ ጌታቸው፡፡
አመሰግናለሁ፡፡ እናንተም አስታውሳችሁኝ ስለመጣችሁ አመሰግናለሁ፡፡ አሁን አሞኛል እኔ ያቅሜን ያህል አገሬንና ህዝቤን አገልግያለሁ፤ ህዝቡ ቢፈልግ ያሳክመኝ፤ አለበለዚያ ስሞት ይቅበረኝ፡፡ ይሄው ነው አመሰግናለሁ፡፡
ምንጭ አዲስ አድማስ