መለስና አልበሽር ሰይጣናቸው ተነስቶባቸው የተኮራረፉ ጊዜ ለተወሰኑ ዓመታት በሁለቱ ፍቅረኛሞች- ጋላባት እና መተማ- ላይ ድንበሩን ጥርቅም አድርገው ዘጉባቸው፡፡ መተማን ለመጀመሪያ ጊዜ የተረገጥኳት ያኔ ከአስራ ሰባት ዓመታት በፊት በ1991 ዓ.ም ነበር፡፡ ያኔ መተማ ህይወት አልባ፣ ፀጥ ረጭ ያለች ከተማ ሆና ነበር፡፡ የመተማን ጎረቤት የሱዳኗን ጋላባትም አሻግሬ አየኋት፡፡ ከመተማ የተሻለ እስትንፋስ ያላት ብትመስልም ፍቅር የተራበች፣ በሯን ገርበብ አድርጋ መተማን የምትጠብቅ ውብ ጎረቤት ሆና ታየችኝ፡፡ መለስና አልበሽርን የተጠናወታቸው ሰይጣን ግን በሁለቱ ህዝቦች ላይ አልነገሰም፤ አይችልምም፡፡ ከሦስት ዓመታት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ መተማን ስረግጥ ግን የመለስና አልበሽር በሽታ ትንሽ ጋብ ብሎላቸው ድንበሩን መልሰው ስለከፈቱት ሁለቱ የጠረፍ ከተሞች እንደገና በደስታ ፈንጠዝያ ሰክረው፤ በፍቅር ከንፈው አገኘኋቸው፡፡
ጋላባት እና መተማን የምትለያያቸው አንዲት ትንሽ ድልድይ ነች፡፡ ከድልድዩ ስር ያለው ገደል በክረምት ወራት ብቻ የትንሽ ወንዝነት ማዕረግ ያገኛል፡፡ በተረፈ ደረቅ ነው… ወንዟ ጥግ ሚጢጢዋ ጣቢያ ላይ የተጎለቱት ሦስት የሀገሬ ወታደሮች ስራ ፈተው ጥርሳቸውን በሱዳን የእንጨት መፋቂያ ይፍቃሉ፡፡ ጥርስ መፋቂያቸውን እንደሰኩ የስራ ባልደረባዬ የነበረችው እንግሊዛዊቷ ሮቤርታ የውጭ ዜጋ ስለሆነች ድልድዩን መሻገር እንደማይፈቀድላት ነገሩን፡፡ ዓይነ-ገቧ እንግሊዛዊት ሮቤርታ ከምር አዘነች፤ ፊቷ ጉበት መሰለ፡፡ የሁለቱን ድሃ ሀገሮች ድንበር አለመሻገሯ ለምን ያን ያህል እንዳስከፋት አሁንም ሳስበው ይገርመኛል፡፡ የሀገሯ ልጅ ሻለቃ ጉዬን ከመቶ ዓመት በፊት በዚያ ድንበር ላይ ችካል ሲተክል እድሜውን ማቃጠሉን አልነገርኳትም፤ በቃ! በዚያ ቅፅበት የድንበርን ነገር ረስቸዋለሁ፡፡ እንደምንም ተደራድሬ አስፈቀድኩላት፤ ቅድመ አያቶቿ ከእንግሊዝ ወደ ስኮትላንድ ሲሻገሩ እንኳ የእሷን ያህል መደሰታቸው ያጠራጥራል፡፡
በደስታ እየፈነደቅን ወደ ጋላባት ገባን፡፡ ጋላባትን ዕምብርቷ ላይ ቁጭ አልኩባት፡፡ ሱዳናዊያን ቆነጃጅቶች ያፈሉትን ግሩም ሻይ ስጠጣ ልዩ ስሜት ተሰማኝ፡፡ ደገምኩት… የሱዳናዊያን ሴቶች ቁንጅና ትንፋሽ ያሳጥራል፤ ልብ ቀጥ ያደርጋል፡፡ የበረሃው ንፋስ ሽው ሲል ድሪያ ቀሚሳቸውን በሚያምረው ገላቸው ላይ ይሸበሽበውና መልሶ ሲበትነው ዓይኔን አብሮ ሲነከራተት ሮቤርታ ሰረቅ አድርጋ አይታ ሳቀችብኝ፡፡ ከድሪያቸው ጋር የሚላፋው ንፋስ የሙዚቃ ቃና የሚፈጥር መሰለኝ…
ሁሌም ከቀኑ ዘጠኝ እስከ አስር ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ በዚያች ድልድይ ላይ ሌላ አስገራሚ ትዕይንት ይታያል፤ በግፊያ ትጨናነቃለች፡፡ ሱዳኖች ቀኑን ሙሉ ሲሰሩ ውለው ወደ መተማ ሲጣደፉ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ በተቃራኒው ወደ ጋላባት ይጎርፋሉ፡፡ ሱዳናዊያን በጋላባት ህግ ክልክል የሆነውን በመተማ የተፈቀደውን አልኮል (አረቂና ቢራ) ለመኮምኮም፤ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ በመተማ ክልክል የሆነውን በጋላባት ባህል የሆነውን ሽሻ ለማጨስ… ሁሉም ፍላጎቱን ከውኖ ምሽት አስራ ሁለት ሰዓት ላይ ወደመጣበት መመለስ አለበት፤ መለስ እና አልበሽር በወንድማማቾቹ ህዝቦች ላይ የጣሉት የመጨረሻው ሰዓት ገደብ አስራ ሁለት ሰዓት ነው፡፡ ያኔ ሱዳናዊው ሞቅ ብሎ፤ ኢትዮጵያዊው በሽሻ ገፅታው ፈክቶ ሲመለሱ በዚያች ድልድይ ላይ ይገናኛሉ፡፡ ከኢትዮጵያዊቷ ቆንጆ ጉያ ስር ያመሸው ሱዳናዊ እና በሱዳናዊቷ ሽቶ ሲነሰነስበት ያመሸው ኢትዮጵያዊ ጎልማሳ ድልድዩ ላይ የአስር ሰዓቱን ድራማ ሁለተኛ ክፍል ይደግሙታል፡፡ ጋላባት በአልኮል ሽታ ስትታፈን መተማ በሽሻና ሽቶ ማዕዛ ትታወዳለች…
አሁን አልበሽር እና የመለስ ወራሽ እነዚህን ዘመን በማይሽረው፣ በልኬት በማይተመን ፍቅር የተቆራኙትን ህዝቦች “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ድንበር ልናሰምርላችሁ ነው፤ የእናንተ እና የኛ የሚል ችካል ልንተክልላችሁ ነው” እያሏቸው ነው፡፡ ያቺ ትንሽ ድልድይ ወደማን እንደምትካለል እንጃ! ባለችበት የጋራ ድንበር ምልክት ሆና ካልቀጠለች የየዕለቱ ትዕይንት ይጠፋል፡፡ በመጨረሻ ግን… እውነት እውነት እላችኋለው፡- ህግ፣ ፖለቲካ፣ ድንበር፣ አይዶሎጂ፣ ሃይማኖታዊ ልዩነት… በጋላባት እና መተማ ሰዎች ልቦና ውስጥ ቅንጣት ታክል ቦታ የላቸውም፡፡ እነዚህ ሁሉ እንቶ ፈንቶዎች ቦታ ያላቸው በመሪዎች ጭንቅላት ውስጥ ብቻ ነው! ህዝቦች ሁሌም በደራ ፍቅር እንዳበዱ ናቸው፡፡ መተማና ጋላባት፡- “ፍቅር እስከ መቃብር!” (Love unto Grave!)….
↧
መተማ እና ጋላባት- ድንበር አልባው የጠረፍ ፍቅር-(ቻላቸው ታደሰ)
↧