የሕግ ከለላ ተሰጥቷቸው ወደ አገራቸው የካቲት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሁለት አመት የዱባይ ስደት በኃላ የተመለሱት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፣ በአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ውስጥ ለተፈጠረው ችግር በተሰጣቸው ጊዜ ገደብ መፍትሔ ማምጣት አልቻሉም ተብለው በቁጥጥር ሥር ዋሉ ሲል ሪፖርተር ዛሬ አስነብቧል፡፡
የዓብይ ኮሚቴው አባል የሆኑት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስቴር አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ በስብሰባው ተናገሩ እንዳለው ሪፖርተር፣ አቶ ኤርሚያስ ወደ አገር ቤት ተመልሰው ሲመጡ መፍትሔ እንደሚሆኑ ታምኖ ነበር፡፡ ነገር ግን መፍትሔ ሊያመጡ ባለመቻላቸው መንግሥት የቤት ገዢዎችን መብት ያስከብራል ብለዋል፡፡
ምሕረት ተሰጥቷቸዋል እየተባለ በአደባባይ የሚነገረው ስህተት መሆኑን አቶ አስመላሽ ተናግረው፣ ነገር ግን ሕግ የጣሰ ይጠየቃል በማለት አስረድተዋል ሲል ሪፖርተር አስነብቧል። በመንግስት መገናኛ ብዙሀን ሳይቀር በወቅቱ መንግስት የህግ ከለላ ሰጥቷቸው ወደአገራቸው ገቡ የተባለውን መንግስት በአቶ አስመላሽ በኩል ክዷል።
በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ የሚመራው የአክሰስ ሪል ስቴት ችግር ፈቺ ዓብይ ኮሚቴ፣ ጥር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. በጉዳዩ ላይ ከቤት ገዢዎችና ከባለአክሲዮኖች ጋር ተወያይቷል፡፡
የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ኑረዲን አህመድ እስካሁን በተሠሩና ማነቆ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ በቀረበው ሪፖርት አቶ ኤርሚያስ ችግሩን ለመፍታት ያቀረቡትን ዕቅድ መፈጸም እንዳልቻሉ ተገልጿል ያለው ሪፖርተር፡፡
ቤት ገዢዎችም የቆየ ብሶታቸውን በምሬት ከማቅረባቸው በተጨማሪ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት እስካሁን ካደረገው የበለጠ ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ በዚህ ውይይት ላይ የተገኙት አቶ ኤርሚያስ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፣ ማክሰኞ ጥር 3 ቀን 2003 ዓ.ም. ከቀኑ 9፡30 ሰዓት ላይ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአራዳ ምድብ ችሎት የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል ብሏል፡፡
ፖሊስ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ በጠየቀባቸው ወቅት በማጭበርበር የተጠረጠሩ መሆናቸውንና 1.4 ቢሊዮን ብር ከቤት ገዢዎች ሰብስበው ያደረሱበት አለመታወቁን፣ እንዲሁም 40 መሬቶች ገዝተው 20 የሚሆኑትን መሸጣቸውን በክሱ ላይ መጠቀሱን የገለጸው ዜናው፤
የአክሰስ ሪል ስቴት መሥራችና የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ኤርሚያስ ለመንግሥት ወደ አገር ቤት ተመልሰው የመፍትሔ አካል ለመሆን ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነት በማግኘታቸው የሕግ ከለላ ተሰጥቷቸው ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል፡፡ ሆኖም የተሰጣቸው የሕግ ከለላ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ በግልጽ የሚታወቅ አልነበረም፡፡ በዚህ መሠረት በሦስተኛ ወገን የቀረቡ 81 ክሶች ለጊዜው እንዲቋረጡ መደረጋቸው ተገልጾ፣ አቶ ኤርሚያስ ሥራቸውን ጀምረው ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ አቶ ኤርሚያስ ዕቅዳቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ በዚህ ዕቅድ ከሁለት የቻይና ኩባንያዎች ጋር ውል ተፈራርመው ወደ ግንባታ እንደሚገቡ፣ ያልተሰበሰበ 300 ሚሊዮን ብር እንደሚሰበስብና ከቦርድ አባላት ጋር በጋራ እንደሚሠሩ ተካቶ ነበር፡፡
አቶ ኤርሚያስ የመፍትሔ አካል ለማድረግ የመረጡት የቻይና ኩባንያ ሲሲኢሲሲ ሊቀመንበር፣ አቶ ኤርሚያስ በቁጥጥር ሥር በዋሉበት ወቅት አዲስ አበባ ገብተው ነበር፡፡ ሊቀመንበሩ አቶ ኤርሚያስ ጋር በመነጋገር የመጨረሻ ውሳኔ ለማስተላለፍ አዲስ አበባ መግባታቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡