የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የኦዲት ግኝት ሪፖርትርን በፓርላማው መድረክ ለመከላከል የሞከሩ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አመራሮችን አስጠነቀቁ፡፡
ዋና ኦዲተር በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ2006 በጀት አፈጻጸምና የክዋኔ ኦዲት በማድረግ ግኝቶቹን በ2007 ዓ.ም. ግንቦት ወር ላይ ለፓርላማው ሪፖርት ያደረገ ሲሆን፣ ሚኒስቴሩ ግኝቶቹን በማስተካከል ረገድ ምን ያህል እንደተጓዘ በፓርላማው የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲያብራሩ ታኅሳስ 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ተጠርተው ነበር፡፡
በዚህ መድረክ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታዎቹ አቶ ታደሰ ኃይሌና ዶ/ር መብርሃቱ መለስ የኦዲት ግኝቱ ላይ ዝርዝር ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የኦዲት ሪፖርቱን ማጣጣል መርጠዋል፡፡ የኦዲት ሪፖርቱ የአንድ ወገን መረጃን ብቻ የያዘ ነው፣ የመውጫ ስብሰባ አልተደረገም በማለት ለመከላከል ሞክረዋል፡፡
በኃፊዎቹ ምላሽ ያልተደሰቱት ዋናው ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ፣ በተለይ የሥራ ኃላፊዎቹ ኦዲቱን የመቀበል ችግር እንዳለባቸው ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሁንም ቢሆን ሒሳብ ነክ የኦዲት ግኝቶች ላይ ዕርምጃ አልተወሰደም፡፡ ማስተካከያ ዕርምጃ አለመውሰድ በሕግ ያስጠይቃል፣ ይህንን ዕወቁ፤›› ሲሉ ባለሥልጣናቱን አስጠንቅቀዋል፡፡
ዋናው ኦዲተር በ2006 ዓ.ም. የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የበጀት አፈጻጸም ላይ ካቀረባቸው ከፍተኛ የሒሳብ ግኝቶች መካከል የመንግሥት ሕግና መመርያ ሳይፈቅድ ለሠራተኛ ማበረታቻ 198,783 ብር አላግባብ መክፈሉ፣ በህንድ አገር ለሚማሩ ሠራተኞች 124,264 ብርና ወደ ውጭ ለሥራና ሥልጠና ለሄዱ ሠራተኞች 18,444 ብር የኪስ አበል መክፈሉ፣ ቢሾፍቱ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት በተዘጋጀ ሥልጠና ላይ ለሠልጣኞች የመኝታና የምግብ ወጪ ከተሸፈነ በኋላ ተጨማሪ 82,950 ብር በድምሩ 424,444 ብር አላግባብ መክፈሉ ይገኝበታል፡፡
ከፌዴራል መንግሥት የግዥ መመርያ ውጭ 1.4 ሚሊዮን ብር ከውል በላይ ለኤምኤች ኢንጅነሪንግ መከፈሉ እንዲሁም ከውል ውጭ 114,614 ብር ለዚሁ ድርጅት መክፈሉን ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም 742.05 ሚሊዮን ብር የምክር አገልግሎትና ግንባታ ግዥ ያለጨረታ መፈጸሙ በኦዲት መረጋገጡን ያስረዳል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዎቹ የኦዲት ግኝቶቹን መንስዔ ከማብራራት እንዲሁም የተወሰደውን ዕርምጃ ከመግለጽ ይልቅ የኦዲት መሥሪያ ቤቱ ማጣጣል ላይ ቢጠመዱም፣ የሥራ ባልደረባቸው የሆኑት የሚኒስቴሩ የፋይናንስ ክፍል ኃላፊ አቶ ሰለሞን ወልደ ጊዮርጊስ ዝርዝር ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል፡፡
ያለጨረታ የወጣው 742.05 ሚሊዮን ብር የፌዴራል የግዥ ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ኤጀንሲ በፈቀደው መሠረት ለቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የወጣ ወጪ መሆኑንና የኢንዱስትሪ ዞን ኮርፖሬሽን ሲቋቋም የሒሳብ ማስረጃ ሰነዶቹም አብረው በመተላለፋቸው ለዋና ኦዲተር በወቅቱ ማቅረብ አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡
የማበረታቻ ክፍያው የተፈጸመው የጥናት ሥራ ላይ ለተሳተፉ 12 የሚኒስቴሩ ሠራተኞች መሆኑን፣ ህንድ አገር እንዲማሩ የተፈቀደላቸው ተማሪዎች በየወሩ 400 ዶላር የኪስ ይከፈላቸው የነበረ መሆኑንና ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ የኪስ ገንዘቡ የተቋረጠ በመሆኑ ችግር ላይ እንዳይወድቁ 124,264 ብር የተከፈለ መሆኑን እንዲሁም የመኝታና የምግብ ወጪ በሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ከተሸፈነ በኋላ ለጥቃቅን ወጪዎች በሚል በቀን 50 ብር በድምሩ 82,950 ብር መከፈሉን ይኽም ተከፋዮቹ ከሠሩት ሥራ አንፃር ያንስ ይሆናል እንጂ የሚበዛ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ወጪዎች በመመርያ የሚደገፉ አለመሆኑን በመርህ ደረጃ እንደሚቀበሉት፣ ነገር ግን ከዋና ኦዲተር ጋር በጋራ እንደሚነጋገሩበት አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡
አቶ ገመቹ ዱቢሶ ግን ይህ እንደማይቻል ይገልጻሉ፡፡ ‹‹የሚገባውን የበላይ አመራር አላስፈቀዳችሁም፡፡ ስለዚህ የሕግ ጥሰት ነው፡፡ በፋይናንስ ሕጉ መሠረት ደግሞ ያስጠይቃል፤›› ብለዋል፡፡
አክለውም ‹‹ትርፍ የተከፈሉ ገንዘቦች መመለስ አለባቸው፡፡ የሕዝብና የመንግሥት ገንዘብ አምስት ሳንቲም ያላግባብ ከተቀመጠው ሕግና የአሠራር ሥርዓት ውጪ ሊወጣ አይችልም፤›› ብለዋል፡፡
የቦሌ ለሚ የኢንዱስትሪ ፓርክን በተመለከተ የግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ኤጀንሲ ፈቃድ እንደሰጠ የሚገልጽ መረጃ በመጨረሻ ላይ የቀረበ ቢሆንም፣ በተሰጠው ፈቃድ መሠረት የወጣ ወጪ ነው ወይ? የሚለውን ዋና ኦዲተር በዚህ ዓመት እንደሚረጋግጥ ገልጸዋል፡፡
ሌሎቹ የሒሳብ ግኝቶች ለኤምኤች ኢንጂነሪንግ የተከፈለውን ጨምሮ ግን መመለስ አለበት ብለዋል፡፡ የቋሚ ኮሚቴው አባል የሆኑት ዶ/ር አድሃነ ኃይሌ ሚኒስትር ዴኤታዎቹ ቃላት ላይ ከሚንጠላጠሉ እውነቱን ቢያስረዱ ሲሉ ገስጸዋቸዋል፡፡ ወ/ሮ ስፍራሽ ብርሃኔ የተባሉ ሌላ የኮሚቴ አባል ደግሞ ‹‹የዚህ መድረክ መሠረታዊ ዓላማ ለመማከርና ለመደጋገፍ እንጂ ቃላትን እየመረጥን አሸናፊን ለመለየት አይደለም፤›› ሲሉ ተችተዋል፡፡
ምንጭ ሪፖርትር
↧
ዋናው ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለሥልጣናትን አስጠነቀቁ
↧