የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ተቀጣጥሏል: መንግስት በመላው ኦሮሚያ ጦርነት ቢያውጅም በባለስልጣኖቹ የህዝብን ክብር የሚነካ ንግግር በመናገር ሊያሸማቅቅ ቢሞክርም፤ ህዝቡ ለመሞት ቆርጦ ፊት ለፊት እየተጋፈጠ ነው።ትላንት ከአዲስ አበባ 60 ኪ/ሜ ወለንኮሚ ተባብሶ መቀጠሉን ብሉምበርግ ዘግቧል።
የብሉምበርግ ዘጋቢ ዊሊያም ዴቪድሰን ከስፍራው እንደዘገበው መንገድ ተዘግቷል፣ የመንግስት ሃይሎችን ጥቃት በማውገዝ፣ በሺ የሚቆጠሩ ፈረሰኞች ወደሆለታ ከተማ ተንቀሳቅሰዋል።
የአዲስ አበባና ኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን አርሶአደሮችን ያፈናቅላል፣ ህገመንገስቱን ጭምር ይጻረራል በሚል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጀመሩትና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እያካተተ የቀጠለው ተቃውሞ፣ በተለይ በአዲስ አበባ አቅራቢያ እየተጠናከረ መገኘቱ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ትኩረት ስቧል።
በአዲስ አበባና በአምቦ መካከል የምትገኘውና ከአዲስ አበባ በ60 ኪሎሜትር ላይ የምትገኘው ወለንኮሚ ከተማ 4 ሰላማዊ ሰዎች ትናንት መገደላቸውን ከስፍራው የዘገበው የብሎምበርግ ዊሊያም ዴቪድሰን፣ ከተማዋ በመከላከያ ሰራዊት መያዟን ገልጿል።
ሰው ተደብቆ እንደሚገኝና በየሰከንዱ የማያቋርጥ ተኩስ ድምፅ እንደሚሰማ የገለጸው ዊሊያም ዴቪድሰን፣ ከጤና ጣቢያና ትምህርት ቤት በስተቀር ሁሉም ተቋማት ላለፉት 4 ቀናት በሰልፈኞቹ ተይዘው መቆየታቸውን ጽፏል።
የቶታል ነዳጅ ማደያ ተሳቢ መኪናን እንዲሁም የዳሸን ቢራ ፋብሪካ የጭነት መኪና በመጠቀም ወደ አምቦ የሚወስደውንና ወደ አዲስ አበባ የሚወስደውን መንገድ የዘጉት ሰልፈኞች የቀበሌ ፅ/ቤት ጠረጴዛዎችንና መደርደሪያዎችን ጭምር ለመንገድ መዝጊያነት እንደተጠቀሙ ከስፍራው ተዘግቧል።
የህዝቡ መገደል ያስቆጣቸው ፈረሰኞች ትላንት ወደ ሆለታ ተንቀሳቅሰው ተቋውሟቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ወደ አዲስ አበባ ለመንቀሳቀስ ሞክረው እልቂት ይከሰታል በሚል ማግባቢያ መመለሳቸው ታውቋል።
ዛሬም በኦሮሚያ ክልል በተቀጣጠለው ህዝባዊ ቁጣ የመንግስት ሃይላት የአጸፋ ጥቃት የቀጠለ ሲሆን፣ ህዝባዊ እምቢተኝነትቱም ጨምሯል። ሱልልታ ላይ በሚደረገው ተቃውሞ የጎጃም በር በመዘጋቱ ወደ ባህርዳር የሚጓዙ የጭነት መኪኖች ይሁን የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ከሱሉልታ ሲመለሱ ውለዋል::ሱሉልታ ላይ ሕዝቡ መንገዱን በመዝጋት ተቃውሞውን እያሰማ የሚገኝ ሲሆን ቀበሌዎችን ወሮ ይዟል::
ተቃውሞው ቀጥሎ በወለጋ ኦብዲ በምእራብ ሸዋ ሜታ ሮቢ እጅግ ከፍተኛ ተቃውሞ በመሰማት ላይ ይገኛል::