በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ሥፍራዎች የአዲስ አበባና የኦሮሚያ የተቀናጀ ማስተር ፕላን በመቃወም የተነሱትን ጥያቄዎች፣ መንግሥት በሠለጠነና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳሰቡ፡፡
ለዴሞክራሲያዊ መፍትሔ ቅድሚያ እንዲሰጥ ያሳሰቡት ፓርቲዎች የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) በተናጠል ባወጡት መግለጫ ሲሆን፣ የኦሮሞ አቦ ነፃነት ግንባር (ኦአነግ)፣ የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር (ኦነአግ)፣ የመላ ኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኦዴፓ) እና የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) ደግሞ በጋራ ባወጡት መግለጫ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ ከተማና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ዞን ከተሞችን ለማቀናጀት የተዘጋጀው የጋራ የማስተር ፕላን ላይ የተፈጠረውን ተቃውሞ አስመልክቶ መግለጫ ማውጣቱን ያስታወሰው ኢዴፓ፣ ‹‹ጉዳዩ መፍትሔ ከማግኘት ይልቅ እየተባባሰና አብዛኛውን የኦሮሚያ ክልል ኅብረተሰብ ባካተተ ሁኔታ መጠነ ሰፊ ተቃውሞ እየታየ ይገኛል፤›› ብሏል፡፡
‹‹በኅብረተሰቡና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መካከል በኦሮሚያ ከተሞች እየታየ ያለው ግጭት የማስተር ፕላኑ ብቻ ሳይሆን፣ በክልሉ ያለው የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብትና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ጭምር ነው፤›› በማለት፣ ‹‹የመብት ጥያቄዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ይፈቱ›› በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ ኢዴፓ አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም ‹‹መንግሥት ሕግንና ሥርዓትን የማስከበር ግዴታ ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች የሚሰጣቸው መልሶች ሕግን የተከተሉ፣ የሰዎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያከበሩ፣ እንደዚሁም በዜጎች ሕይወትም ሆነ አካል ላይ ጉዳት የማያደርሱ መሆን ይገባቸዋል፤›› ሲል ኢዴፓ አሳስቧል፡፡
ከዚህ በፊት በማስተር ፕላኑ ጉዳይ ላይ ኢዴፓ ባወጣው መግለጫ የተፈጠረውን ችግርና የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ ገለልተኛ ኮሚቴ እንዲቋቋም መጠየቁን አስታውሶ፣ ‹‹ሆኖም መንግሥት ጥሪያችንን በቸልተኝነት በማለፍ ጉዳዩ እልባት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ አሁንም ለችግሩ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ከመሠረቱ የሚያጣራ ገለልተኛ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንዲያጣራና የደረሰበትን ውጤት ለሕዝቡና ለፓርቲያችን ይፋ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፤›› በማለት ጥያቄውን ለመንግሥት አቅርቧል፡፡
በተመሳሳይ ኢራፓ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ጥበብንና ዕውቀትን ለመገብየት ሲሉ በተለያዩ ደረጃዎች የትምህርት ገበታዎች ላይ የተሰማሩ ሴትና ወንድ የኦሮሚያ ቡቃያዎችንና ሌሎችንም መሰል እንቡጦች፣ ሕገ መንግሥቱ ያረጋገጠላቸውን መብት ተጠቅመው በሰላማዊ መንገድ ቅሬታዎችን ባሰሙት፣ እንዲሁም በወላጆችና በኅብረተሰቡ ላይ መንግሥት እስካሁን የወሰደውና በመውሰድ ላይ የሚገኘውና ነገም ሊወስድ ያለው ያልተመጣጠነ የኃይል ዕርምጃ ሕገ መንግሥታዊ ስለማያስብል የሚነቀፍ ድርጊት ነው፤›› በማለት ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅትም ሆነ ባለፈው ዓመት በማስተር ፕላኑ ሰበብ የታሰሩ የኦሮሚያና ሌሎች ወጣቶችና ንፁኃን ዜጎች በሙሉ እንዲፈቱ፣ በእነዚህ ወቅቶች ውድና ብርቅ ሕይወታቸውን ያጡት የስም ዝርዝራቸው እንዲታወቅ፣ አግባብ ያለው ካሳም እንዲታሰብላቸውና የኃይል ዕርምጃ የወሰዱትም ለሕግ ይቅረቡ፤›› በማለት ኢራፓ ጠይቋል፡፡
‹‹መንግሥት ለኢንዱስትሪያላይዜሽን በመውተርተር ላይ በሚገኝበት በአሁኑ ወሳኝ ወቅት፣ የአገራችንን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችንና አፍራሽ ክስተቶችን በወታደራዊ ዕርምጃ ለመፍታት መሞከር ‘በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ’ ከሚለው አልፎ፣ የአገሪቷን ዕጣ ፈንታ ወዳልተፈለገ ጠርዝ እንዳይገፋና ዓለም አቀፋዊም ሆነ አካባቢያዊ ጣልቃ ገብነቶች የጋራ ቤታችንን በርግደው እንዲገቡ በር ከፋች ከመሆን፣ መንግሥት እንዲጠነቀቅ፤›› በማለት ኢራፓ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
‹‹ኅዳር 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ለገዢው ፓርቲና ለመንግሥት ማስተር ፕላኑን በተመለከተ ግልጽነት ስለሚጎድለው ጥቅሞቹንና ጉዳቱን እንዲሁም ጭራሽ መቅረቱንና ወደፊት የሚተገበር መሆኑን፣ ለኦሮሞ ሕዝብ ግልጽ እንዲያደርጉና በዚህ የተነሳ አንድም የኦሮሞ ዜጋ ሕይወት እንዳያልፍ አንስተን ተወያይተንበታል፤›› ያሉት አራቱ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ አራቱ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ በውይይቱ የተገኙ የኦህዴድ አባላትም ‘ማስተር ፕላኑ የኦሮሚያን ሕዝብ የሚጎዳ ከሆነና ሕዝባችን የማይፈልገው ከሆነ በኃይል በሕዝቡ ላይ የሚጫን ሊሆን እንደማይገባ ይፋ አድርገው ወደፊትም ሕዝቡን እናወያያለን’ የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡
‹‹ይህንን ተቃውሞ ያባባሰው ጨፌ ኦሮሚያ በመጀመርያ መደበኛ ስብሰባው ያወጣውና ሕዝቡ ያልመከረበት የኦሮሚያ ማስተር ፕላን አዋጅ በመሆኑ፣ በአሁን ጊዜ መላው የኦሮሞ ተማሪዎችና መላው የኦሮሞ ሕዝብን ቁጣ የቀሰቀሰ በመሆኑ አዋጁ በአስቸኳይ እንዲሻር፤›› በማለት በጋራ መግለጫቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
‹‹ከሁለት ዓመት በላይ የኦሮሞ ተማሪዎችን ሕይወት የቀጠፈው የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን፣ መላው የኦሮሚያ ሕዝብ ተቃውሞውን ያሰማበት በመሆኑ ዕቅዱ ቆሞ ጉዳዩ በሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ለሕዝቡ ይገለጽ፤›› በማለት አሳስበዋል፡፡
ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ