አርብ ታህሳስ 1/2008
በዛሬው እለት በአንዋር መስጊድ ከጁምዓ ሰላት በኋላ ቦንብ መፈንዳቱ ታውቋል፡፡ በፍንዳታው የተጎዱ ሙስሊሞችም አሉ፡፡ ለፍንዳታው ተጠያቂ አካል ማን አንደሆነ እስካሁን የተገለፀ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ይህ ፍንዳታ በ1987 መንግስት በአንዋር መስጊድ ግጭት አስነስቶ በርካታ የሙስሊም መሪዎችን፣ ኡለማዎችንና ወጣቶችን ያሰረበትን ክስተት ያስታውሰናል፡፡ በአራት አመት የትግል ሂደታችን መንግስት ሰላማዊ ትግላችንን ፈር አስለቅቆ በሀይል ለመጨፍለቅ ያደረጋቸውን ሙከራዎችን እንደህዝብ ተከላክለናል፣ አክሽፈናልም፡፡
የመንግስት የደህንነት አካላት ከአወሊያ ጀምረው በየመስጊዳችን መሰግሰግ ጀምረው ነበር፡፡ ይህንን የሚያውቁት ኮሚቴዎቻችን በግልፅ ‹‹በመካከላችን የምትገኙ የደህንነት አባላት›› እያሉ መልእክቶቻቸውን ያደርሱ ነበር፡፡ ከአወልያ ጀምሮ የደህንነቱ ክፍል ኮፍያ፣ ጥምጣምና አባያ ገዝቶ በርካታ ተቀጣሪዎቹን በመስጊድ እንዲውሉ ካደረገ ውሎ አድሯል፡፡ ትንኮሳዎቹም ዛሬ የተጀመሩ አይደሉም፡፡ ብልሆቹ ኮሚቴዎቻችን በሰጡት አመራር አንድ ቅጠል ሳይበጠስ የማበጣበጥ ሴራዎች ከሽፈዋል፡፡ ተቃውሞው ወደ አንዋር መስጊድ ከተሸጋገረበት ጊዜ ጀምሮ ‹‹ከዛሬ ነገ ብጥብጥ በተነሳ!›› በሚል እኩይ አላማና ጉጉት በአንዋርና ኑር መስጊዶች ዙሪያ ባሉ ህንፃዎች ላይ ካሜራ ጠምደው “የብጥብጥ ማስረጃ” ለመቅረፅ ለብዙ ጊዜ ቋምጠዋል፡፡ ከተቃውሞ ፊት ለፊትም የአንበሳ አውቶቡሶችን እንዲሰበሩላቸውና እንዲቀረፁ ፊት ለፊት ለመደርደርም ሞክረው ነበር፡፡ ነገር ግን ህዝበ ሙስሊሙ መንግስት የሚያስብበትን አእምሮ በሚገባ አውቋልና የ1987 ክስተት በፍፁም እንዳይደገም በጥንቃቄ ተጉዟል፡፡ ይህ ቢሆንም የራሱ ደህንነቶች በሰሩት ‹‹መኪና የማቃጠል››፣ ‹‹ባንዲራ የማቃጠል›› እና ‹‹በቪዲዮ የመቅረፅ›› ስራዎችን ሰርቷል፡፡ በእነዚህ በሙስሊሙ መካከል በተሰገሰጉ ደህንነቶችና ካድሬዎች ከተሰሩት ደባዎች ግን በሀምሌ 11ዱ ‹‹የጥቁር ሽብር›› ጥቃት ወቅት ያስነሱት ትንኮሳና የተሰነዘረው ጥቃት ግን ወደር አልነበረውም፡፡ በተለያዩ ክልሎችም የወንድሞቻችንን ህይወት የቀጠፉና አካልን የጎዱ ጥቃቶችን ከጁሙአ ሰላቶች መልስ ፈጽመዋል፡፡
‹‹መንግስት በዚህ ትግላችን ከተጀመረ አራተኛ ዓመት በሆነበትና ሀገሪቱ በድርቅና በተቃውሞ እየተናጠች ባለችበት ወቅት የሙስሊሙን ትግል ጥላሸት በመቀባት ትኩረትና አጀንዳን ለማስቀየር አይሞክርም›› የሚል የዋህነት የለንም፡፡ ይህንን የምንለው መንግስት እኩይ ተግባር ለማድረግ ምክንያት (Motive)፣ የመፈፀም ብቃት (Access)፣ አጋጣሚ (Opportunity) እና ያለፈ ሪኮርድ (Past Record) ስላለው ነው፡፡ ከዚህ በፊት በይፋ ያልተዋወቁና ቅፅበታዊ የተቃውሞ መርሀግብር እንኳ ሲኖር በተሰገሰጉት ደህንነቶቹ ‹‹ወረቀት ይዘህ ነበር›› በማለት ሲያስሩ እንደነበር የምናውቀው ነው፡፡ በዚህ ሳምንት በተለይም በአንዋርና በኑር መስጊድ ለየት ባለ መልኩ የፖሊሶች ቁጥር ጨምሮ እንደነበርም መረጃዎች አሉ፡፡
አንድ ነገር ግልጽ ነው፡፡ ስሌቶችን በማስላትና ሴራን በማጠንጠን በቀላሉ ሕዝብን ማታለል አይቻልም፡፡ ከቅርብ ታሪካችን ተነስተን ‹‹ዋናው ተጠርጣሪያችን መንግስት ነው›› ብንልም ሌላ አካላት ሊያደርጉት አይችሉም የሚል እምነትም የለንም፡፡ ሁሉንም ግን አላህ ያውቃል! ዛሬ የደረሰውን ጥቃት ከማውገዝ ባለፈ ግን ሀይማኖታችንንና መስጊዶቻችንን የመጠበቅ ሃላፊነት ከማንም በፊት የራሳችን ሙስሊሞች ሃላፊነት ነው፡፡ አሁንም ህዝበ ሙስሊሙ በየመስጊዶቹ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አጥብቀን እናሳስባለን፡፡ መስጊዶቻችንን እና አጠቃላይ ተቋሞቻችንን እኩይ ዓላማዎችን አንግበው ከሚመጡ አካላት የመከላከሉ ስራ የሰላማዊ ትግላችን አንዱ አካል ነው፡፡ የሙስሊሞች ሰላማዊ ሂደት የሚያጠለሹ ስራዎችን በአይነቁራኛ የመጠበቅ ሀላፊነትም አለብን፡፡ በየመስጊዶቻችንና በየተቋሞቻችን የተሰገሰጉ የመንግስት ደህንነትና ካድሬዎችን የማጋለጥ ሀላፊነትም በሁላችንም ላይ እንዳለብን ልንዘነጋው አይገባም፡፡ አላህ በጥቃቱ የተጎዱትን ጤናቸውን ይመልስላቸው ዘንድ እንመኛለን!
ብሄራዊ ጭቆናን አንሽከምም!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር
↧
በአንዋር መስጊድ የደረሰው ፍንዳታ በሙስሊሙ ላይ የተቃጣ እኩይ ድርጊት ነው! የሴራው አቀናባሪዎች ስሌትም አይሰራም!(ድምጻችን ይሰማ)
↧