Quantcast
Channel: Kalkidantube
Viewing all articles
Browse latest Browse all 3774

ፍትሕን በብሔር ግንኙነት የሚሸጡና ለወሲብ ድርድር የሚያቀርቡ ሙያተኞች እንዳሉ ተነገረ

$
0
0

ከፖሊስና ከማረሚያ ቤት በበለጠ ፍርድ ቤት ለሙስና የተጋለጠ መሆኑ ተጠቆመ

በኢትዮጵያ የፍትሕ ተቋማት ውስጥ ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውን ጠብቀው ሕዝባዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ ታማኝ የፍትሕ ባለሙያዎች ያሉትን ያህል፣ ፍትሕን በገንዘብ የሚቸበችቡ፣ የተሰጣቸውን የሙያ ሥነ ምግባር ዘንግተው ዳኝነትና

ፍትሕን በአገር ልጅነት ወይም በብሔር ግንኙነት የሚሸጡና ለወሲብ ድርድር የሚያቀርቡ እንዳሉ ተነገረ፡፡
d11be8ab966081bf919d3439c92cfca1_L
የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዓሊ ሱሌይማን፣ ጥቅምት 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ‹‹በኢትዮጵያ ፍትሕ ዘርፍ ሙስናን ለመከላከል የሚያስችሉ፣ የፍትሕ ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥና አፈጻጸም አመላካቾች›› በሚል ርዕስ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ እንደተናገሩት፣ የተወሰኑ በፍትሕ ተቋማት ውስጥ ያሉ ሙያተኞች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ የሚገኙና ሙስና የሚፈጽሙ ናቸው፡፡ ሙስና በተንሰራፋበት በፍትሕ መድረክ ላይ ዜጐች በእኩልነት አይስተናገዱም፡፡ በተለይም ለነፃ ገበያ ዋነኛ መሠረት የሆነው የኮንትራት አስተዳደር ከቅጥፈት፣ ከአድልዎና ከአላስፈላጊ ባህሪዎች ነፃ ሆኖ ዳኝነት መስጠት በማይቻለበት ሁኔታ፣ አገሪቱ የምትመኘውን የኢኮኖሚ ዕድገትና የሚታሰበውን ያህል ኢንቨስተሮችን መሳብ እንደማይቻል ኮሚሽነሩ አብራርተዋል፡፡ ይኼንን እውነታም ሕዝቡ ጠንቅቆ እንደሚያውቀው አክለዋል፡፡

ሙስናን የመታገያው የመጨረሻው መተማመኛ ተቋም የፍትሕ ሥርዓቱ በሙስና ከተፍረከረከ፣ አጠቃላይ የፀረ ሙስና ትግሉ አደጋ ላይ መውደቁ የማይቀር መሆኑን አቶ ዓሊ አስረድተዋል፡፡ የፍትሕ ተቋማት ከዘርፈ ብዙ የሙስና ዓይነቶች ካልፀዱ፣ አሠራራቸው ለሕዝብ ግልጽ ካልሆነ፣ በሕግ ከተቀመጠው የአሠራር ሥርዓት ያፈነገጡ በሕግ ተጠያቂ ካልሆኑ፣ ችግሩ በፍትሕ ተቋማት ብቻ እንደማይፈታና ወደ አገራዊ አደጋ እንደሚሸጋገር ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽነሩ እንዳሉት፣ ሕግ መተርጐም ለዳኞች የተሰጠ ኃላፊነት ነው፡፡ ነገር ግን ዳኞች ሕግን በነፃነት እንዳይተረጉሙ ለሕዝብ ተቆርቋሪ በመምሰል የግል ፍላጐትን ለማሟላት በዳኝነት ሥራ ላይ የሚደረገው ጣልቃ ገብነት ሊወገድ ይገባል፡፡ የኮሚሽነር ዓሊን ንግግር ተከትሎ በፍትሕና ሕግ ሥርዓት ምርምር ኢንስቲትዩት ባልደረቦች ከላይ በተገለጸው ርዕስ ያዘጋጁትን ጥናት አቅርበዋል፡፡

ወ/ሪት ማዕረግ ገብረ እግዚአብሔር፣ አቶ አሮን ደጐልና ዶ/ር ደጀኔ ግርማ የተባሉት የጥናቱ አቅራቢዎች፣ ጥናታቸውን ያደረጉት ለሙስና ዋና ተጋላጭ ናቸው ባሏቸው ፍርድ ቤት፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ፖሊስና ማረሚያ ቤቶች ላይ ነው፡፡ ጥናቱ ከድሬዳዋ ውጪ በቆዳ ስፋታቸውና በሕዝብ ብዛታቸው ቀዳሚ ናቸው ያሏቸውን ኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎች፣ ውስጥ ያሉ ዋና ዋና የፍትሕ አካላትን ማካተታቸውን አስረድተዋል፡፡

ዋና ዋና ያሉዋቸው አራቱ የፍትሕ አካላት ሊፈጽሟቸው የሚችሉ የሙስና ድርጊቶች ጉቦ፣ ሥራን መበደል፣ ምዝበራ፣ በሥልጣን መነገድና የማይገባ ሀብት ማካበት መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ የፍትሕ አካላቱ ለሙስና ተጋላጭ የሚያደርጓቸው ምክንያቶች ዕውቀትና ክህሎት ማነስ፣ የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ማነስ፣ ነፃና ገለልተኛ አለመሆን፣ ሰፊ ሥልጣን መኖር፣ ግልጽ የሆነ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት አለመኖር በዋናነት የገለጿቸው ናቸው፡፡

ከወንጀለኞች ጋር በቅርበት መሥራት፣ ለኃላፊዎች ያላቸው መታየት ዝቅተኛ መሆን፣ ወንድማማችነት (ጥፋትን መሸፋፈን)፣ ተግባራቸው ለሕዝብ ግልጽ አለመሆን፣ ፖሊሶችን ለሙስና ከሚያጋልጡ ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የማረሚያ ቤቶች ጥበት፣ በታራሚዎች አያያዝ ላይ የሠራተኞቹ ግንዛቤ አናሳ መሆን፣ የማረሚያ ቤት ሠራተኞች ለሕግ ተገዢ አለመሆን፣ የጥበቃ ሠራተኞች ከታራሚዎች ጋር የሚፈጥሩት ከሙያ ውጪ የሆነ ቅርበትና ወዳጅነት ደግሞ ማረሚያ ቤትን ለሙስና ተጋላጭ ከሚያደርጉት ምክንያቶች ጥቂቶቹ መሆናቸውን ጥናት አቅራቢዎቹ ገልጸዋል፡፡

የፍርድ ቤትን አሠራር ቀልጣፋ ማድረግ፣ የፍርድ ቤት ሠራተኞችን ሥነ ምግባር ማሻሻል፣ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ፣ ግልጽ አሠራር ማጐልበት፣ የዳኝነትን ነፃነት ማረጋገጥ፣ ከገቢ ጋር ተያያዢነት ያላቸውን ለሙስና የሚያጋልጡ ምክንያቶችን ማስወገድ፣ ተቋማትን ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች ማደራጀት፣ የመረጃና የሰነድ አያያዝ ሥርዓት ማጠናከር፣ የክትትል ሥርዓት መዘርጋት፣ የጥቅም ግጭት ማስወገድና ሌሎችንም ለሙስና በር የሚከፍቱ ምክንያቶች በጥናቱ መለየታቸውን አቅራቢዎቹ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፣ የፌደራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የዓቃቤ ሕግና የተለያዩ ተቋማት ተወካዮች የቀረበውን ጥናት አድንቀው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ምንጭ ሪፖርተር ተጻፈ በ ታምሩ ጽጌ


Viewing all articles
Browse latest Browse all 3774

Trending Articles