ትላንት፣ ነሐሴ ፳፭ ቀን ማለዳ ያረፉት የኢሉባቦር እና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሥርዐተ ቀብር፣ ዛሬ ዕለት ከረፋዱ 4፡00 ላይ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
አስከሬናቸው ከናሽናል ሆስፒታል ከደረሰበት የዋዜማው ምሽት ጀምሮ ሊቃውንቱ ቅኔ ማኅሌት፤ ቀሳውስቱ ሰዓታት በመቆም የሚገባውን ሥርዐት ሲያደርሱ አድረዋል፡፡ ንጋት ላይ ሥርዐተ ቅዳሴው በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እየተመራ ተከናውኗል፡፡ ጸሎተ ፍትሐቱ በዐውደ ምሕረት እንደተፈጸመ ከቅዱስ ላሊበላ ደብር እንዲሁም ከአዲስ አበባ አድባራት እና ገዳማት በመጡ ሊቃውንት ብፁዕነታቸው የሚዘክሩ ቅኔዎች ቀርበው ተሰምተዋል፡፡
ብፁዕነታቸው መንፈሳዊ፣ ቅን፣ ታዛዥ እና ጸሎተኛ እንደነበሩ የተናገሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ለአገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን በአበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለሌላው አርኣያ በመኾን ዘወትር የሚጠቀሱ አባት ናቸው፤ ብለዋል፡፡
የቀድሞ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩትን የብፁዕ አቡነ ፊልጶስን ዜና ሕይወት እና ሥራዎች አጭር ታሪክ በንባብ ያሰሙት፣ ከብፁዕነታቸው በኋላ የወቅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የኾኑት ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ናቸው፡፡
………………………………………………………….
– ፩ –
የኢሉባቦር እና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ ከአባታቸው ከአቶ ፈለቀ ለውጤ፣ ከእናታቸው ከወ/ሮ አዛልነሽ ሙሉ በ1928 ዓ.ም. በወሎ ክፍለ ሀገር በላስታ ቡግና አውራጃ ሠራብጥ ካህናተ ሰማይ ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ ተወለዱ፡፡
ብፁዕነታቸው በተወለዱበት በካህናተ ሰማይ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ መምሬ ኃይሉ ከተባሉ መምህር ንባብ እና ዳዊት፣ ሰዓታት እና አምስቱን አዕማደ ምስጢር ተምረዋል፤ እንዲኹም ወደ ገነተ ማርያም በመሔድ፣ መሪጌታ ኃይለ ማርያም ከሚባሉ ፀዋትወ ዜማን ተምረዋል፡፡ ወደ አርካ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አምርተው ከአለቃ ኢሳይያስ ጾመ ድጓን በመማር ላይ እንዳሉ በግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ማዕርገ ዲቁናን ተቀብለዋል፤ በኋላም ወደ ትውልድ ቀበሌአቸው ተመልሰው ጥቂት እንደቆዩ በደሴ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ከመምህር ገብረ እግዚአብሔር መጻሐፍተ ሐዲሳትንና መጻሕፍተ መነኰሳትን ተምረዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በፍጹም ሐሳባቸው ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የመረጡበት መንገድ ምንኵስና በመኾኑ ዳግም ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተመልሰው ሥርዐተ ምንኵስናን ፈጽመዋል፡፡ በተከታታይም ማዕርገ ቁምስና ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ከተሰጣቸው በኋላ ገደሚት ከምትባል ገዳም ገብተው ለጥቂት ጊዜ እንዳገለገሉ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከአለቃ በዛብህ ወንድም ጋር ወደ ዞብል ከመምህር ወልደ ሰንበት ሰዋስወ ቅኔን ተምረዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በአዲስ አበባ የወንጌል ትምህርት በማስተማር ሰፊ አገልግሎት ከመስጠታቸውም በላይ፡-
የመድኃኔዓለም በጎ አድራጎት እየተባለ ይጠራ የነበረውን ማኅበር አደራጅተዋል፤
የተማሪዎች አንድነት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበርን አቋቁመዋል፤
ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳስ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ኾነው ይሠሩ በነበረበት ወቅት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር አስተዳዳሪ ኾነው እንዲሠሩ ተሾመዋል፤
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ፣ ለምግባረ ሠናይ የትሩፋት ሥራ ቅድሚያ እና ትኩረት የሚሰጡ አባት በመኾናቸው በምግባረ ሠናይ የአረጋውያን እናቶች እና አባቶች መርጃ እና መረዳጃ ማኅበርን በማቋቋም በርካታ ችግረኞች እንዲረዱ አድርገዋል፡፡
– ፪ –
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ፣ በመጀመሪያ የአለቃ በዛብህ ወንድም በአሠሩት በሐውልተ ስም መድኃኔ ዓለም ገዳም አለቃው እንዳረፉ ተተክተው ማገልገል ይችሉ ዘንድ በገዳሙ ማኅበር ተመርጠው ለብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ቀርበው የገዳሙ መምህር እና አስተዳዳሪ ኾነው እንዲሠሩ ተሠይመዋል፡፡
ከዚኽ በኋላ የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም እና ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ኾነው አገልግለዋል፡፡ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር፣ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪ በመኾን ሠርተዋል፡፡
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመንፈሳዊ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ፣ የሐረርጌ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ በመኾን ከቦታ ወደ ቦታ በመዘዋወር ሠርተዋል፡፡
ብፁዕነታቸው ባላቸው ከፍተኛ የአስተዳደር ብቃት በቅዱስ ፓትርያርኩ መልካም ፈቃድ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኾነው በትጋት አገልግለዋል፡፡ በሀገረ ስብከቱ ቆይታቸው በአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራት የስብከተ ወንጌል እጥረት በነበረበት ቦታ በመዘዋወር አገልግሎቱ በስፋት እንዲዳረስ አድርገዋል፡፡ ጠዋት ጠዋት በየትምህርት ቤቱ እየተዘዋወሩ የግብረ ገብ ትምህርት በማስተማር የስብከተ ወንጌል ማኅበራትን እያቋቋሙ ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት እና ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡
– ፫ –
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ፣ በቁምስና ደረጃ የኢሉባቦር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው እንዲያገለግሉ በተፈቀደላቸው መሠረት፤ በ1986 ዓ.ም. ወደ ኢሉባቦር ተጉዘው የቀድሞው መንበረ ጵጵስና በሚገኝበት መቱ ከተማ ላይ ኾነው ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ጀመሩ፡፡
ይህ በዚኽ እንዳለ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ጵጵስና ምርጫ አፈጻጸም የወጣውን መመዘኛ አሟልተው በመገኘታቸው ኅዳር 4 ቀን 1987 ዓ.ም. “ጳጳስ ዘኢሉባቦር” ተብለው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ አንብሮተ እድ ተሾሙ፡፡
ብፁዕነታቸው በመጀመሪያ በቁምስና ደረጃ ወደ ኢሉባቦር ሀገረ ስብከት ሲመጡ መንበረ ጵጵስናው ፈርሶ በጅማ ሀገረ ስብከት ሥር እንዲተዳደር ተደርጎ ነበር፤ መንበረ ጵጵስናውን የማደራጀት እና የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤት የማቋቋም ሥራ የብፁዕነታቸው ተቀዳሚ ተግባር ነበር፡፡
የሀገረ ስብከቱን ካህናት እና ምእመናን አስተባብረው ገንዘብ በማሰባሰብ በርካታ የልማት ሥራዎችን ሠርተዋል፤ ከነዚኽም መካከል በዘመናዊ ፕላን የተሠራው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሕንፃ ተጠቃሽ ነው፡፡
ብፁዕነታቸው ወደ ኢሉባቦር ሲመጡ የነበሩት የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ብዛት 217 ሲኾን በዘመነ ጵጵስናቸው ባደረጉት የማስተባበር ሥራ በአኹኑ ወቅት 320 አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ይገኛሉ፡፡ የአብያተ ክርስቲያኑ ቁጥር ሊያድግ የቻለው፤ ብፁዕነታቸው በየወረዳው ሐዋርያዊ ጉዞ እያደረጉ በየመቃብር ቤቱ እያደሩ ስብከተ ወንጌልን በመስጠት፣ የፈረሱ እንዲታደሱ፣ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያን እንዲታነፁ በማድረግ ታላላቅ ተግባራትን በማከናወናቸው ነው፡፡
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ ከቁምስና ደረጃ እስከ ማዕርገ ጵጵስና ድረስ በአህጉረ ስብከቱ በቆዩባቸው ኻያ ኹለት የሥራ እና የአገልግሎት ዘመናቸው በጸሎት እና ቡራኬአቸው የተመረቁ ጠቅላላ አብያተ ክርስቲያናት ብዛት 93 መድረሱ ተረጋግጧል፡፡
በመንበረ ጵጵስናው አካባቢ ከሚገኙት አድባራት መካከል የፈለገ ሕይወት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን የአንድነት ገዳም ኾና እንድታገለግል አድርገዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ግንቦት 22 ቀን 1922 ዓ.ም. ባደረገው ምልዓተ ጉባኤ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ፣ በኢሉባቦር ሀገረ ስብከት ሥራቸው ላይ የጋምቤላ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው ደርበው እንዲሠሩ በመወሰኑ ኹለቱን አህጉረ ስብከት አጣምረው በመምራት የተጣለባቸውን ሓላፊነት በብቃት ተወጥተዋል፡፡
ብፁዕነታቸው፣ የጋምቤላ ሀገረ ስብከትን በሊቀ ጵጵስና እንዲመሩ ከተመደቡበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡ ከዚኽም መካከል ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን በመጋበዝ የክልሉን ብሔረሰብ ከፕሬዝዳንቱ ጀምሮ በማጥመቅ ወደ ክርስትና ሕይወት እንዲገቡ አድርገዋል፤ በክልሉም የልማት ሥራዎች ለማፋጠን ተንቀሳቅሰዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በጎደሬ ወረዳ ከስምንት ያላነሱ አብያተ ክርስቲያንን አሳንፀዋል፤
በ1996 በጋምቤላ ክልል በተከሠተው የእርስ በርስ ግጭት የልጆቼን ችግር አብሬ መቋደስ አለብኝ በማለት ከቦታው ድረስ በመገኘት ሕዝቡን በማጽናናት የማረጋጋቱን ሥራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አከናውነዋል፤ በቦታውም ዘላቂ ሰላም እስከሚሰፍን ድረስ በማስተባበር ድርሻቸውን በሚገባ ተወጥተዋል፡፡
– ፬ –
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጰጳስ፣ በነዚኽ ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን ክብር እና አገልግሎት ከተሠየሙ ጀምሮ ባላቸው የሥራ ልምድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት እና በመልካም አስተዳደር ሲመሩ ቆይተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው ባላቸው የብዙ ዓመታት የሥራ ልምድ በመጠቀም፣ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ መልካም ፈቃድ ከሐምሌ 24 ቀን 1998 ዓ.ም. ጀምሮ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የቤተ መጻሕፍት ወመዘክር እና የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት ሊቀ ጳጳስ ኾነው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ከዚኽም ሌላ፤
ቅዱስ ሲኖዶስ ሚያዝያ 21 ቀን 2002 ዓ.ም. ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ለሦስት ዓመታት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ኾነው እንዲሠሩ ተደርጓል፡፡ በዚኽ ከፍተኛ ሓላፊነታቸው፣ በቤተ ክርስቲያን ተጠግተው በሥራ አጥነት የሚቸገሩትን አቅም በፈቀደ መጠን ሥራ እንዲያገኙ በማድረግ የመምሪያ እና የድርጅት ሓላፊዎች ጋር በመተባበር የዋና ሥራ አስኪያጅነት ታላቅ ሓላፊነታቸውን በምስጋና አጠናቀዋል፡፡
– ፭ –
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በቅዱስ ሲኖዶስ አባልነታቸው በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው በዓለም አቀፍ ጉባኤያት ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ብፁዕነታቸው፣ መላ ዘመናቸውን ለሰው የሚራሩ ትሑት እና ደግ የትሩፋት አባት እንደነበሩ በርካታ የድኻ ልጆችን በማሳደግ በማስተማር ራሳቸውን ከመርዳት አልፈው ለሀገር፣ ለወገን የሚጠቅሙ ልጆችን አፍርተዋል፡፡
ብፁዕነታቸው፣ በጊዜ ሳይገደቡ ዘወትር የጸሎት መጻሕፍት ከእጃቸው የማይለይ ለጸሎት የተጉ የትሩፋት አባት ነበሩ፡፡
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲኽ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ሲታከሙ ቆይተው ነሐሴ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በ79 ዓመታቸው ከዚኽ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
የቀብራቸው ሥነ ሥርዐትም፤
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የየመምሪያ እና የድርጅት ሓላፊዎች እና ሠራተኞች፣
የአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣
ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣
የኢሉባቦር እና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ተወካዮች
ወዳጅ ዘመድ ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት በአዲስ አበባ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ነሐሴ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ተፈጽሟል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ የብፁዕነታቸውን ነፍስ ከቅዱሳን ጻድቃንና ሰማዕታት ጋር ይደምርልን፡፡ አሜን፡፡
ምንጭ ሓራ ዘ ተዋህዶ