ትናንት ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት፤ ከተከሰሱበት የሽብርተኝነት ወንጀል በነጻ ከተሰናበቱት አምስት ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆነውና የቀድሞ የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው ሀብታሙ አያሌው ከታሰረበት ከቂሊንጦ እስር ቤት በዛሬው ዕለት መውጣት እንዳልቻለ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የሀብታሙ ባለቤት ወ/ሮ ቤተልሄም እንደገለጸችው ከሆነ፤ ለፍቺ የሚያስፈልጉ ሕጋዊ ሂደቶችን አስተካክለው ከዛሬ ከሰዓት ጀምሮ በቂሊንጦ ቢገኙም ባለቤቷ መውጣት አልቻለም፡፡ ወ/ሮ ቤተልሄም አያይዛም እስከ ምሽት 12፡45 ሰዓት ድረስ በቂሊንጦ የጊዜ ቀጠሮ እስር ቤት በር ላይ ቆመው የሀብታሙን መውጣት ቢጠባበቁም ሀብታሙ ሳይመጣ በመቅረቱ ወደመኖሪያ ቤታቸው መመለሳቸውን አስረድታለች – ‹‹ሰኞ ይወጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን›› በማለት፡፡
በትናንቱ የፍርድ ቤት ውሎ፤ የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አመራር የነበረው ዳንኤል ሺበሺ፣ የአረና ፓርቲ አመራር አባል አብርሃ ደስታ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባል የሺዋስ አሠፋና አብርሃም ሰለሞን ክሱን መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ፣ በዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ አብረው የተከሰሱ አምስት ተከሳሾች ግን እንዲከላከሉ መወሰኑ ይታወሳል፡፡