በኦሮሚያ ክልል መንግስት ጦር ቢያዘምትም ሕዝቡ ሰላማዊ ጥያቄውን ከመጠየቅ አላቆመም ” የታሰሩት ይፈቱ፣ ወታደሮች ከትምህርት ቤቶች ይውጡ፣መግደል አቁሙ፣የገደሉ ለፍርድ ይቅረቡ ” የሚሉ ጥያቄዎች የተለያዩ አካባቢዎች ዛሬም የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች እንደቀጠሉ መሆናቸውን ከተለያዩ ከተሞች የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ ።
ከአምቦ ከተማ ባለፈው ሃምሌ ወር ታስሮ በአዲስ አበባ እስር ቤት ውስጥ ታሞ ሆስፒታል ሲደርስ ህይወቱ ያለፈው ተማሪ አብደታ ኦላንሳ ቀብር ዛሬ በአምቦ ከተማ ተፈጽሟል። የአንቦ ህዝብ በነቂስ የወጣበትን ቀብር ሥነ ስርዓቱን ለማስተጓጎል የጸጥታ ሃይሎች ድብደባና እስር ፈጽመዋል ተኩሰው የገደሉትም አለ ሲል ቪኦኤ ዘግቧል።
በስልክ ቪኦኤ ያነጋገራቸው የአንቦ ነዋሪ አቶ ጉቱ ትናንት ማታ የወጣቱን አስከሬን ለመቀበል በወጣ ህዝብ ላይ የጸጥታ ሃይሎች ድብደባ አድርሰዋል። ወደሰማይ ሲተኩሱም ነበር። አንድ ሰው በጥይት ተመትቶ ተገድሉዋል ብለዋል።
የአምቦው ነዋሪ አስከትለውም ዛሬ በቀብሩ ላይም እንዲሁ የከተማው ነዋሪ በብዛት ወጥቶ እንዳይቀብረው ለማስተጉዋጎል ወታደሮች በተለይ ወጣቶችን መኪና ላይ እየጫኑ ወስደዋቸዋል ብለዋል። ወደቀብሩ ጉዞ ላይ የነበረ ወጣት በጥይት መገደሉን ገልጸዋል።
ትናንትና ደግሞ በአምቦ ዩኒቨርስቲ አዋሮ ግቢ አጠገብ የአንድ ወጣት አስከሬን ተገኝቱዋል ብለዋል አቶ ጉቱ
የአምቦ ወረዳ ኣስተዳዳሪ ኣቶ አሰፋ ሂርኮ አምቦ ውስጥ ተገደሉ የተባለውን አስተባብለዋል ብሏል ቪኦኤ።
ከድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ቪኦኤ ባገኘው መረጃ ደግሞ ፌደራል ፖሊሶች የተማሪዎች መኝታ ቤቶች እየገቡ ጭካኔ የተመላበት ድብደባ አካሂደዋል ብዙ መቶዎች አስረው ወስደዋል ሲል ስሜን አትግለጹ ያለ ተማሪ ተናግሯል። ተማሪዎች ያሉትን ለማጣራት ወደከተማዋ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ደውሎ እንዳልተሳካለት ቪኦኤ በዘገባው አመልክቱዋል
በምዕራብ አርሲ ሻሸመኔ ደግሞ የከተማው መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች “የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው ምክንያት የታሰሩ ተማሪዎች ይፈቱ” “ ግድያው ይቁም “ በማለት ትናንትናና ዛሬ ሰልፍ ወጥተዋል ሲሉ “ ስማችንን እንዳትገልጹብን” ያሉ ተማሪዎች ለሬዲዮው ገልጸውላታል።
በሰላም ነበር ሰልፉ የሚካሄደው የመንግሥት ሃይሎች በተኑት ፡ የተወሰኑ ተማሪዎች ተደበደቡ ፡ የታሰሩም አሉ ያለው ተማሪ እኔም ራሴ ከተደበደቡት አንዱ ነኝ ብሏል።
“የሃሮማያ እና የጅማ ተማሪዎች እንዲሁም በአምቦ ተማሪዎች መገደላቸውን በመቃወም ፡ ድርጊቱ ይቁም ትግላችን ይቀጥላል ብለን ድምጻችንን ስናሰማ ነበር” ሲል ገልጿል።’የቪኦኤን ሙሉ ዘገባ ያዳምጡ።
↧
በኦሮሚያ ከተሞች ዛሬም ተቃውሞ ቀጥሏል-VOA Amharic
↧