በወሬ እና በይስሙላ አካሔዶች የተሳሳተ ምስል እየፈጠረ ራሱን እንደ ለውጥ አራማጅ እና መሪ በመስበክ የሥልጣን ወራቱን እያራዘመ የሚገኘው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ “ፓትርያርኩን ሰርፕራይዝ እናድርጋቸው” በሚል ከሀገረ ስብከቱ ሒሳብ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንዲኾን ማድረጉ ተገለጸ፡፡
“የፓትርያርኩን የተጓደሉ የመኖርያ ቤት ዕቃዎች ለማሟላት እና ለመተካት” በሚል ከሀገረ ስብከቱ ተቀማጭ ብር 586‚000 ወጪ የተደረገ ሲኾን ግዥው አስቀድሞ ያልታቀደና በጀትም የተያዘለት እንዳልነበር ታውቋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በተደረገው የሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር ጉባኤ ስብሰባ፣ አዲስ አበባ የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት መኾኑን በመጥቀስና “ሥራ አስኪያጃችንን ስላስቀጠሉልን ሰርፕራይዝ እናድርጋቸው” በሚል ግፊት አስቀድሞ ተሰብስቧል በተባለው ፕሮፎርማ መሠረት ግዥው በተጠቀሰው ወጪ እንዲካሔድ መወሰኑ ተመልክቷል፡፡
እንደ ቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ፣ እንዲህ ባሉ ግምታቸው ከፍተኛ በኾኑ ወጭዎች የፈራሚው ሊቀ ጳጳሱ አልያም የፓትርያርኩ ፈቃድና መመሪያ ቢያስፈልግም ግዥው በዋናነት በሥራ አስኪያጁ አመንጪነትና በአድርባይ ሓላፊዎች ግፊት በታቀደ “ሰርፕራይዝ” በመከናወኑ፣ የሀገረ ስብከቱ ተቀማጭ ሒሳብ ያለበላይ ተቆጣጣሪ በየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ አማሳኝ እና ዓምባገነናዊ አካሔድ እየባከነ ለመኾኑ አረጋግጧል፡፡
“አዲስ አበባ የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ስለኾነ” የሚለው የሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ድንጋጌ በአስተዳደር ጉባኤው ስብሰባ ተነሥቶ ውሳኔውን ሕጋዊ ለማስመሰል ቢጠቀስም ክፋቱ “የየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የሥልጣን ማራዘሚያ መርፌ መኾኑ ነው፤” ያሉ የመረጃው ምንጮች፣ የቅዱስነታቸውን መኖርያ ጨምሮ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩን በባለቤትነት የማስተዳደር ሓላፊነት ያለው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት እንደኾነና በጉዳዩ እንዳልተማከረ፣ የሚያውቀውም ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
“የፓትርያርኩን መኖርያ ቤት ማሟላት የቤተ ክህነቱ ድርሻ ነው” በሚል ለተነሣው ሐሳብም “ከእዚያ ጋር መነካካት አያስፈልግም፤ የራሱ ጉዳይ” የሚሉ በእብሪት የተሞሉ ምላሾች ከአድርባዮቹ ሓላፊዎች መሰጠታቸው ታውቋል፡፡
ግዥውን እንዲያከናውን በተቋቋመው ሦስት የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች ባሉበት ኮሚቴ፣ ለየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ቅርበት እንዳላቸው የሚነገርላቸው የፓትርያርኩ ረዳት የኾኑት መነኮስ እንዲጨመሩ መደረጋቸው፣ ‘ሰርፕራይዝ ነው’ የተባለውን ምስጋና አወሳስቦታል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ከጥቅምት 25 ቀን ጀምሮ ወደ ምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት መጓዛቸውን ተከትሎ፣ “ከዓዲ ግራት መልስ ሳያውቁ ቤታቸው ተቀይሮ ማግኘት አለባቸው” በሚል ከኢትዮ ሴራሚክስ፣ ከግሎሪየስ፣ ከአዲስ ዲኮር፣ ከዋሪት፣ ከዋው፣ ከዴሉክስ ፈርኒቸርስ በርካታ የግል መገልገያ ዕቃዎች ተሸምተው በጨረታ ያሸነፈ ነው በተባለው ድርጅት እንዲገጠሙ ተደርጓል፡፡
በተከናወነው ግዥ÷ የሳሎን፣ የመኝታ እና የመታጠቢያ ቤት እንዲኹም የመመገቢያ አዳራሽ ዕቃዎች የተካተቱ ሲኾን ከእነርሱም መጋረጃ እና የወለል ምንጣፎች፤ ወንበሮች እና ጠረጴዛዎች፤ አልጋ እና ፍራሽ፤ ጃኩዚ እና ቴሌቭዥኖች እንደሚገኙበት ተገልጧል፡፡
የፓትርያርኩ የመኖርያ ቤት መገልገያዎች፣ ከአያያዝ ጉድለት ይኹን ከጊዜ ብዛት “አርጅተዋል፤ ቆሽሸዋል፤ በልዘዋል፤ ተነቃቅለዋል” ቢባል እንኳ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት፣ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት ተጠሪ እንደ መኾኑ መጠን የገንዘብ እንቅስቃሴውን ማወቅና በጉዳዩም መማከር ነበረበት፡፡
ባለመደረጉ፣ የየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ያልታቀደና ያልተፈቀደ የሥልጣን ማራዘሚያ ‘ሰርፕራይዝ’፣ በአወዛጋቢ የሥራ አስኪያጅነት ምደባው ሳቢያ ካለፈው ዓመት የካቲት ወዲኽ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ ጋር ተቃውሶ የቆየውን መዋቅራዊ ግንኙነት የበለጠ እንደሚያባብሰው ተጠቁሟል፡፡
በርግጥ፡-
ከሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅነት ጋር በዋና ጸሐፊነት ደርቦ በያዘው የገነተ ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ ደብር፣ ያለሀገረ ስብከቱ ዕውቅና እና ያለሊቀ ጳጳሱ ፈቃድ በሕገ ወጥ የዲዛይን ክለሳ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ የግንባታ ወጪ ልዩነት ያለበትን ሕንፃ በማስቀጠል ባካበተው ዳጎስ ያለ ሀብት ቀጣይ የቢዝነስ ፕላኑን እያማተረ ላለው የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፤
ያለሊቀ ጳጳሱ መመሪያና ያለአስተዳደር ጉባኤው ውሳኔ÷ በአጥቢያ ሠራተኞችና ካህናት ዝውውር፣ ቅጥር እና የ“ጠብቀኝ፣ አትንካኝ” መደበኛ አምኃዎች ምዝበራውን ላጧጧፈው የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፤
ከአወዛጋቢ ምደባውና ከሙስና ወንጀሉ ጋር በተያያዘ፣ በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወቅት የተፈጠረበትየተጠያቂነትና የመወገድ ስጋት አልፎኛል በሚል በቀጣይ የበርካታ አድባራት አለቆችን በማዘዋወር ወንጀሉን ለመሸፈንና ምዝበራውን ለመቀጠል ለቋመጠው የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፤
የፓትርያርኩ የብር 586‚000 የሥልጣን ማራዘሚያ እና የምስጋና ሰርፕራይዝ ወጪ ላያስደነቅ ይችል ይኾናል፤ ሀገረ ስብከቱ ግን በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኝ ብሎጎች ጭምር በሚታገዘው የየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ከተግባር የራቀ የለውጥ አራማጅነትና መሪነት ዲስኩሩ ሽፋን፤ እንዲኹም ሕግና ደንብ በማይገዛው አማሳኝና ዓምባገነናዊ አካሔዱ በቀጣይ ብክነት እንዳለ ተረጋግጧል!!
ምንጭ ሐራ ዘተዋሕዶ