የዓለማችን ሁለተኛው ጸረ ፕሬስ መንግስት የሆነው ኢህአዴግ ጋዜጠኞችን እስር ቤት በማጎር የሚረካ አልሆነም። እናም ከጥቂት ተልመጥማጭ የህትመት ውጤቶች በቀር የሰላ ሂስ በማቅረብ የሚታወቁትን ጋዜጣና መጽሄቶች በጉልበት ዘግቶ ጋዜጠኞችንም ለስደት ዳረገ። የረጂዎቹ ምዕራባውያን በትር እስኪያርፍበት።
አምባገነኑ አገዛዝ ከዓመት በኋላ ደግሞ የበቀል በትሩን በመምዘዝ… በተሰደዱ ጋዜጠኞች ላይ 18 ዓመት ለመፍረድ ዓይኑን አላሸም።
የህትመት ውጤቶቹ ተዘግተው… ጋዜጠኞቹ እስኪሰደዱ ለአንዲት ቀን እንኳ ትችት አቅርበው የማያውቁት የገዢው ፓርቲ ሎሌ ጸሀፊዎች “ጋዜጠኞቹ ወደ ሀገር አይመለሱም” ብለው መደምደም ከጀመሩበት ጥቂት ወራት ወዲህ… የ”ጭቃ ጅራፋቸውን” መምዘዝ ጀምረዋል። በፌስቡክ የለቀቁትን ጽሁፍ ለ”ሎሚ” እና ሌሎች መጽሄቶች እያቀበሉ… ገንዘብ በመቀበል ” ሌላ መጽሄት ላይ ስለምሰራ እባካችሁ ስሜን አታውጡ” እያሉ ሲማጸኑ የኖሩት እንደ ጌታቸው ይመር (የአሌክስ አብርሀም እውነተኛ ስም ነው) የቀድሞ ከፋዮቻቸውን ከሀገር መራቅ ተከትለው “የእስር ፍርዱ ያንሳቸዋል” የሚል ዘመቻ እንዲጀምሩ ታዘው “ሥራቸውን” እያጣደፉት ነው።
ጭምብላቸው ወልቆ እስኪወድቅባቸው ድረስ “መንግስት በጋዜጠኛ ላይ 18 ዓመት መፍረዱ ልክ ነው” በማለት የአምባገነኖች “የቁርጥ ቀን ልጅ” መሆናቸውን በማሳየት የደጅ ጥናታቸውን ልክ “እያስመሰከሩ” ነው።
ለመሆኑ ይህን የግፈኛውን አገዛዝ የ18 ዓመት እስራት ፍርድ “ልክ ነው” እያለ በመዘመር… የአገዛዙን ሎሌዎች በፊታውራሪነት በመምራት ላይ የሚገኘው ጌታቸው ይመር (አሌክስ አብርሀም) ማን ነው? ለስደት ከተዳረጉ ጋዜጠኞች አንዱ የሆነው ኢብራሂም ሻፊ አህመድ እንደሚከተለው ገላልጦ… እርቃኑን ያሠጣዋል።
…………… ……………….. ………………. ……………………..
“ሰው ያለቦታው………”
ደርሶ ሁሉም ቦታ አዋቂ……..ሁሉም ቦታ እኔን ስሙኝ……….እኔ ብቻ አውቅላችኋለው…….እኔ…..እኔ…..እኔ…..የሚሉ ሰዎች ብዙም ምቾት አይሰጡኝም፡፡ የእኔ መንገድ ትክክለኛው መንገድ ነው ብለው ከደመደሙም የበለጠ ምቾት ይነሱኛል፡፡ በጉዳዩ ላይ ያላቸው አውቀት ጥራዝ ነጠቅ ሆኖ “እኔን ብቻ ስሙኝ…….” የሚሉ ከሆነ ብልግናቸው ያሳፍረኛል፡፡ ይህን የሚያደርጉት ደግሞ ከዚህ በፊት የሰበሰብኳቸው አሁን እንደፈለግሁት የምነዳቸው ተከታዮች አሉኝ በሚል ድፍረት ከሆነ ጤንነታቸውም ያጠራጥረኛል፡፡ የዚህ ሁሉ የምሬት መግቢያ መነሻዬ አሌክስ አብረሃ ገፅ ላይ “የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ሩጫ” የተመለከተን ፅሁፍ ማንበቤ ነው፡፡ ፅሁፉ ኢትዮጵያ ቡና ላይ የተነጣጠረ ይመስል እንጂ ሁሉም የኢትዮጵያ ቡድኖችን፣ የስፖርት አመራሮችን፣ ደጋፊዎችን፣ ተጨዋቾችን፣ አሰልጣኞችን፣ አርቢቴሮችን እና የስፖርት ስርዐት ጠባቂዎችን ይመለከታል፡፡ ስለስፖርቱ መረጃን የሚያቀርቡ ሰዎችን በገደምዳሜው ይነካካል፡፡ ስለስፖርት……በተለይ በባለሙያዎች ስለሚደረግ (Professional) እግርኳስ ባህሪ እና በውስጡ ስለሚገኙ እምቅ ስሜቶች ሳይተነትን ወደዘለፋ ይጓዛል፡፡ ፀያፍ ቃላትን ደራርቶ ባደባባይ አፍ ተካፈቱኝ ብሎም ይጋብዛል፡፡ ርካሽ ተወዳጅነት ያስገኙልኛል ያላቸውን ነጥቦች (Elements) ከስድብ ጋር አጅሎ ሰጥቶናል፡፡ ሆኖም ከእርሱ ለስፖርቱ እንቀርባለን ብለን የምናስበው እኛ በዚህ መንገድ ፅሁፉን እንወቅሰዋለን፡፡
አትዋሽ
“ገና ከመጀመሪያው ለቡና የስፖርት ክለብ ገቢ ማሰባሰቢያ መኖሩን ስሰማ ቲሸርቱን ልገዛ ጎራ ብዬ ነበር…….ግን ምን ያደርጋል ከቡድኑ አርማ ይልቅ ፊት ለፊት በትልቁ የቢራ ፋብሪካ ስም የታተመበት ቲሸርት ለብሸ እንደምሮጥ ሲነገረኝ ተውኩት”
ኢትዮጵያ ቡና ለተጨዋቾች የመኖሪያ ካምፕ እና የልምምድ ማዕከል ማስገንቢያ የደጋፊወች ሩጫ እንዳለ ካሳወቀ ሶስት ወራት ሆኖታል፡፡ አንተ (አሌክስ) “ገና ከመጀመሪያው” ከተጓዝክ ሶስት ወራት ተቆጥረዋል ማለት ነው፡፡ ያኔም የመሮጫ ቲሸርቱን አሳይተውኽ ንቀሃቸው እንደተመለስክ እየነገርከን ነው፡፡ ሆኖም እውነታው ይሄ እንዳልሆነ ስለሩጫው በቅርብ የተከታተሉ ሁሉ ያውቁታል፡፡ የሩጫው አዘጋጆች ጋር ፅፌም የተረዳሁት የቲሸርቱ ዲዛይን ሩጫው ሊከወን ሶስት ቀናት እሰኪቀሩት ምስጢር ነበር፡፡ በሶስቱ ወራት ውስጥ ቲሸርቱ ምን መምሰል እንዳለበት፣ የቡድኑ ደጋፊዎች ስታዲየም ሲመጡም እንዲለብሱት እና ጥራቱን በተመለከተ እርማት እና ማስተካከያ ሲሰሩ ነበሩ፡፡ አንተ ግን ቲሸርቱን ቢያንስ ከሶስት ወራት በፊት አይቼዋለሁ ብለህ ትዋሻለህ፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ቁጥሩ ብዙ ነው ብልህ አስበህም አሁንም “የርካሽ ተወዳጅነት” ስሌትህን ወደዚሁ አምጥተህ “ልሮጥላችሁ ነበር…….ሆኖም ሀበሻ ቢራ ከለከለኝ” ልትል ትፈልጋለህ፡፡ መዋሸት ምንም ኃጢያት እንዳልሆነ ማን እንደመከረኽ……የትኛው መፅሐፍ ላይ እንዳነበብከው እንጃ፡፡ ብቻ ባደባባይ ብዙ ግዜ ትዋሻለህ፤ ጌታቸው ይመር የተባለ፣ ኢትዮጵያን ሊያሰደምም የሚችል ገጣሚ እየመጣ ነው…..አንብቡት አልክ፡፡ እኛም ምን አይነት ጥሩ ገጣሚ እና ቅዕናት የሌለው በጎ አስተዋዋቂ መጣ ብለን ጥቂት ግጥሞች ኮሞኮምን፡፡ ሆኖም ጌታቸውም አንተው………አሌክስም አንተው ሆነህ ራስህን እያሞካሸህ እንደሆነ ተረዳን፡፡ ይሁን ቢያንስ ግጥም አስነበበን እንጂ አልጎዳንም ብለን ተውነው፡፡ አንድ ሌሊት ላይ በዐሉ ግርማን ሙልጭ አድርገህ በስድብ አጥረገረከው (አሁንም እኔን በዚህ ወይም በሌላ አካውንትህ እንደምትዘልፈኝ እጠብቃለሁ)፡፡ ወዳጅህ አፈንዲ ሙተቂ “አሌክስን ደውዬለት ነበር……መጠጥ ቀማምሶ ስለነበር በቸልተኝነት የፃፈው ነው” አለን፡፡ አንተ ግን አፈንዲንም ባደባባይ ካድከው፡፡ “ሳይለኝ ነው ያልኩት” እንዲል በሚያስገድድ ቃና አስተባባዬ ጓደኛህን “እኔ ነኝ ውሸታሙ” አስባልከው፡፡ ግን ሆድህ ያባውን እና ብቅል ያወጣውን ፅሁፍህን አጠፋሃው፡፡ ሳትቀማምስ የፃፍከው ፅሁፍ ቢሆን አስከመጨረሻው በፃፍከው በፀናህ እና ፅሁፉም ባልጠፋ ነበር፡፡ ያኔም ከመታዘብ ውጪ ምንም አላልንም፡፡ ብቻ ባደባባይ ሌላ በጓዳ ሌላ ሰው መሆንህን በግልፅ ተረዳንበት፡፡ ውሸትህ እንዲህ እየተጎተተ እዚህ አድርሶኃል……….ያላየኸውን አየሁ…………ያልነበርክበትን ነበርኩ እስከሚያስብልህ፡፡ በዚህን ያህል መጠን ባደባባይ የሚዋሽን ሰው “ሰክረው የሚወላገዱና አላፊ አግዳሚው ላይ ቢራ የሚረጩ ነበሩ!” የሚል ምስክርነትን ሲሰጥ ማን ይቀበለዋል? የፎቶ ማስረጃዎችን ጠቅሼ በሩጫው ላይ ብዙ ስርዐት አስከባሪዎች አይቻለሁ የምለው እኔ አፍራለሁ፡፡ ምክንያቱም ስደተኛ ነኝ እና በቦታው አልነበርኩም፡፡ ሆኖም የፎቶ ማስረጃዎቹን አምኜ እና የሃገሬን ስርዐት አስከባሪዎች ባህሪ ተንትኜ “ይህን ሲያደርጉ ማንም ዝም አይላቸውም፤ ስለዚህ አላደረጉትም” የሚለውን ባምን ይሻለኛል፤ ያንተ ተደጋጋሚ ውሸት ለዚህ ድምዳሜዬ መድረሻ ዋነኛው ሰበብ መሆኑን ግን አትዘንጋ፡፡
ሁለት ፍትህ ለአንድ ጉዳይ (Double Standard)
“የቢራ ፋብሪካ አርማ ታትሞብኝ በየመንገዱ መጠጥ ከማስተዋውቅ ኢትዮጵያ ቡና የሚባል የስፖርት ክለብ ገቢ አጥቶ ቢበታተን እመርጣለሁ”
ኢትዮጵያ ቡና ተበታትኖ የማየት ፍላጎትህ ጥልቀት ካስቀመጥከው አስቂኝ ምክንያት ጋር ሲደመር “ሰው ያለቦታው…….” ያስብላል፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ቡና የቢራ ፋብሪካን ለማስተዋወቁ የመጀመሪያው አይደለም፤ የመጨረሻውም አይሆንም፡፡ ከሃገራችን እንጀምር፡፡ ከተመሰረተ 80 ዓመታትን ያስቆጠረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በየዓመቱ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ፋብሪካ የሚደረግለት የገንዘብ ድጋፍ አለ………ዳሽን ቢራ………ሀረር ቢራ………..(አሁን ስያሜው ተቀይሯል) ተብለው የተቋቋሙ ቡድኖችም አሉ፡፡ ፋብሪካዎቹ የኢትዮጵያ እግርኳስ እንዲያድግ ለሚያደርጉት አስተዋፅዖ ይመሰገናሉ እንጂ ምነው በእነርሱ ከምንረዳ “ተበታትነው በቀሩ” አያስብልም፡፡ ለትርፍ የተቋቋሙ ድርጅቶች በማህበራዊ ዘርፍ ተሳትፎን ያድርጉ ስንል ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ እና መንገድ ሲገነቡ የምንሰጣቸውን ያህል አክብሮት የእግርኳስ ቡድኖችንም ሲረዱ እንሰጣቸዋለን፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውጤት አስመዝግቦ ከበደሌ-ሄይኒከን ቢራ የ24 ሚሊዮን ብር ስፖንሰር ሲያገኝ ዝም ያልክ ልጅ ዛሬ “ኢትዮጵያ ቡና ለምን በሀበሻ ቢራ ስፖንስር ተደረገ?” ማለትህ ሁለት ፍትህ ለአንድ ጉዳይ (Double Standard) ይሆንብኃል፡፡
ክልከላ መፍትሄ አይደለም
“ስታዲየሙ ቀስ በቀስ ትልቅ የቢራ ገበያ እየሆነ ነው”
ለእኔ ቀላሉ ነገር “ቢራን አትጠጡ…..ሃራም ነው!!!” ማለትን ነው፡፡ ቢያንስ ሀይማኖቴ የሚያዘኝ እና ከሀይማኖቴ ቀኖናዎች አንዱ ይሄ ነው፡፡ ሆኖም ነገሩን በሌላ መንገድም ማየት አለብን፡፡ ነብያችን ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በመጀመሪያ ስለ መጠጥ ክልከላ ዱዐ (ፀሎት) አደረጉ እንጂ “አትጠጡ” ብለው አልከለከሉም፡፡ በጊዜ ሂደት ዱዐቸው ተቀባይ ሆኖ የቁርዐን አያ (አንቀፅ) ወረደላቸው፡፡ መጠጥም ክልክል ሆነ፡፡ አየኽ አሌክስ ሀይማኖቴ ያስተማረኝ ይሄንን ነው፡፡ አትከልክለው፣ አትጠየፈው፣ አታግልለው፣ አትዝለፈው፣ አታንኳሰው…………አስተምረው!!! ከሁሉም ከሁሉም ግን ዱዐ አድርግለት፡፡ ስለዚህም የስታዲየሙ ዙሪያ “ትልቅ የቢራ ገበያ” የሆነው እነዚያ ሰዎች ከአንተ አይነት አስመሳይ ሲሸሹ ነው፡፡ከውሸታሙ የበለጠ እንደትልቅ ሃጢያተኛ ተቆጥረው ምሳር ስለበዛባቸው ነው፡፡ የተፈጥሮ ባህሪ ነው እና አምሳያቸውን ፈልገው የተቀላቀሉት፡፡ የተሰበሰቡበትን ቦታ ምሽጋቸው ያደረጉት፡፡ ግን እኛ አስመሳዮቹ ብንጠጋቸው፣ ብንመክራቸው እና ፀሎት ብናደርግላቸው ከስህተት መንገድ እንታደጋቸዋለን፡፡ መቼም እነዚህን ሰዎች ማስታወቂያ አታሏቸው የገቡ “አይረቤ” ናቸው ብለህ እንደማትንቃቸው ተስፋን አደርጋለሁ፡፡
“ውበትን ፍለጋ”
“ማንኛውም የስፖርት ክለብ ህይወት አይደለም……..ከትውልዱ ኑሮ ሞራል እና ጤንነት ቀጥሎ የሚመጣ ሁለተኛ ነገር ነው”
ለእግርኳስ የሚሰጠው ትርጓሜ እና ክብር ከዚህም በታች ወርዶ ስለተመለከትኩ ብዙም አልገረምም፡፡ እግርኳስን 22 ተጨዋቾች አንዲት ቅሪላን እንደሚያባሩ………….በዙሪያቸው የከበቧቸው ሰዎች ደግሞ እሱን እየተመለከቱ እንደሚያውካኩ………ተደርጎ ሲሳል አስተውያለሁ፡፡ አሌክስ አብርሃን ጨምሮ እግርኳስን ስለሚዘግቡ ሰዎች “በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኛ ለመሆን መስፈርቱ ምንድን ነው?” ብለው ሲያፌዙም ታዝቤያለሁ፡፡ እግርኳስ ግን በእንደ ቢል ሻንክሌይ አይነቱ ታላቅ አሰልጣኝ እና አሰላሳይ “እግርኳስ የህይወት እና ሞት ጉዳይ አይደለም፤ ከዚያም በላይ እንጂ” ሲባልም አንብቤያለሁ፡፡ ለበርካታ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ቡድናቸውን የቢል ሻንክሌይ ትርጓሜ ይገልፅላቸዋል፡፡ ለቅዱስ ጊዮርጊስም…….ለሁሉም የኢትዮጵያ ቡድኖች ደጋፊዎችም ይህ ገለፃ ይመስጣቸዋል፡፡ ለቡድናቸው ህይወታቸውን የከፈሉ ደጋፊዎች አውቃለሁ፡፡ ጤናቸው ተቃውሶ (አንዳንዶች የአይናቸው ብርሃን ማየት ተስኖት እንኳን) ቡድኔን ልከታተል ብለው ስታዲየም ውሰዱኝ የሚሉ ሰዎችን እኔው ራሴ አይቻለሁ፡፡ አንተም ከፈለግህ ቀጣይ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታን ፕሮግራም ልብ ብለህ ስታዲየም መጓዝ ትችላለህ፡፡ እንደኔው በአይንህ አይተህም ተገርመህ ትመለሳለህ፡፡ ስለምን ዓይነት ሞራል እንደምታወራ እንጃ እንጂ ብዙ ግዜ 25000 ደጋፊ እንድላይ ተቀምጦ፣ የተለያየ ቡድን ደግፎ፣ ተቃራኒ ሆኖ ተበሻሽቆ እንዲሁም በቃላት ተቆራቁዞ በስተመጨረሻም በሰላም ወደቤት የሚጓዘው ስታዲየም ውስጥ ነው፡፡ ይሄ ህዝብ የገንዘብ እንጂ የሞራል ድሃ አይደለም፡፡ ከጤንነቱ ቡድኑን………..ከህይወቱ ክለቡን የሚያስቀድምም ብዙ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኛ ለመሆንም የዚህን ህዝብ ስሜት እንዳንተው ሳይዘባርቁ በትክክል ማስቀመጥ የመጀመሪያው መስፈርቱ ነው፡፡
አሁንም “ማስ ሰፖርት?”
“ስፖርት ትውልድን ከዚህ ዓይነት ፀያፍ የመጠጥ ሱስ ትውልድን ለማዳን አንዱ መንገድ ነበር የሚመስለኝ”
ስፖርት ሲባሉ በልጅነታቸው ከሰሙት የተስፋዬ ገብሬ “ስፖርት ለጤንነት……ለምርት……ለወዳጅነት……..ስፖርት…….ለአእምሮ ማንቂያ……ስፖርት ለጤና መጠበቂያ………..” ዘፈን ያልተላቀቁ ብዙ ሰዎች አሉ………አንደኛው አሌክስ ነው፡፡ ተስፋዬ ጥሩ ዘፈንን ዘፍኗል፡፡ በወቅቱ ስፖርት የሁለት ርዕዮተዓለም ትርጓሜዎች ከወዲህወዲያ ያላጉት ስለነበር ትርጓሜውም አብሮ ይንገላታ ነበር፡፡ ተስፋዬ ኢትዮጵያ ከምትከተለው ርዕዮተዓለም (Communism) ተነስቶ ዘፈኑን አቀነቀነው፡፡ ልክም ነበር፡፡ አሁን ግን ስፖርት ከእነዚህ ዋጋዎች አልፎ የመልቲ ቢሊዮን ዶላር ንግድ ሆኗል፡፡ እግርኳስም ያንን መንገድ ተከትሏል፡፡ ተጨዋቾቹም የሙሉ ሰዐት ስራቸው ኳስን መጫወት (Professional) ሆኖ ክፍያቸውም በዚያው መጠን አድጎላቸዋል፡፡ ታላላቅ ኩባንያዎችም የእግርኳስ ጨዋታን ስፖንሰር ያደርጋሉ፡፡ የቢራ ፋብሪካዎች እዚህ ውስጥም ይደመራሉ፡፡ ስታዲየም በመደበኛ ስራቸው ታላላቅ የምንላቸው ሰዎች እንኳን ደስ የሚሉ “ህፃን” የሚሆኑበት ቦታ በመሆኑ ኃላፊነት እንዲሰማቸው ማገዝ እንጂ ክልከላ የለም፡፡ ስለዚህም ቢራ ይሸጣል……….ለሲጋራ ማጨሻ የተከለለ ቦታም አለ፡፡ እዚህ ጋር ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንዱ መፈለግ ሲሆን ሁለተኛው ኃላፊነት ነው፡፡ የማይፈልግ አይጠጣም እንዲሁም አያጨስም፡፡ ድርጊቱን የሚከውን ደግሞ በኃላፊነት እንዲያደርገው በስፖርት ጠባቂዎች (Stewards) ይታገዛል፡፡ ለዚህም ነው የዓለምዓቀፉ እግርኳስ አስተዳዳሪ ኣካል (ፊፋ) እና የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር (ዩኤኢፋ) ጨምሮ ብዙ ታላላቅ ውድድሮች በቢራ ፋብሪካዎች ስፖንሰርነት የሚደረገው፡፡ ታላቁ የዓለም ዋንጫ ከቡድዋይዘር ሲቀጥልም ከዓምስቴል ቢራ ጋር ወዳጅ ነው፡፡ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ በሄይኒከን ስፖንሰር ይደረጋል፡፡ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ቢያንስ ለስምንት ዓመታት ወጪው ሲሸፈንለት የነበረው በካናዳው ካርሊንግ ቢራ ነው፡፡ ማክኤዋንስ፣ ካራቢስ እና ቻንግ የተባሉ ቢራዎችም የተለያዩ የዓለማችን ጎበዝ ክለቦችን ስፖንሰር ያደርጋሉ፡፡ ያንተ “የሆነው ሆኖ የስፖርት አፈርድሜ አንደበላች እና በአሁኑ ሰዐት የስፖርት ክለቦቻችን ከዓለምዓቀፍ የስፖርት ዓላማ ርቀው የቢራ ፋብሪካዎች የማርኬቲንግ አንድ ክፍል ከመሆን” ትንታኔ የመረጃ እና እውቀት እጥረት መሆኑንን እታዘባለሁ፡፡ ቡድኖቻችን ዓለምዓቀፉን መንገድ ተከተሉ እንጂ በተቃራኒው አልተጓዙም፡፡ አሁንም እነዚሁ ቡድኖቻችንን የስፖንሰሮችን ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም……ኢትዮጵያ ቡናም…….ብሔራዊ ቡድኖቻችንም…..ሁሉም ቡድኖቻችን የስፖንሰሮችን ድጋፍ ይሻሉ፡፡ በወልጋዳ ብዕር ተሸብረው ስፖንሰር አድራጊዎች የኢትዮጵያን እግርኳስ ከመርዳት መታቀብም የለባቸውም፡፡ ባለፈው ግማሽ ምዕተዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ያለምንም ልዩነት በደስታ የፈነጠዘው እና ፊቱ ላይ ፈገግታ የታየው ብሔራዊ ቡድኑ ደቡብ አፍሪካ ላይ ለተዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ሲበቃ መሆኑን ማን ይዘነጋል?