ከሚያዝያ 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት 18 ወራት በእስር ላይ የነበሩት ጦማሪያን፣ ጥቅምት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. የተመሠረተባቸውን የሽብር ድርጊት ወንጀል ክስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ተወሰነ፡፡
ከታሰሩ ጀምሮ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የመሠረተባቸውን ክስ ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ በነፃ እንዲሰናበቱና በዕለቱ እንዲፈቱ ትዕዛዝ የሰጠው ጦማሪያን አቤል ዋበላ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ አጥናፍ ብርሃኔና በሌለችበት የተከሰሰችው ሶሊያና ሽመልስ ናቸው፡፡ ጦማሪ በፈቃዱ ኃይሉ የተከሰሰበት የወንጀል ሕግ ተቀይሮ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን እንደገለጸው፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ያቀረባቸው የሰውም ሆኑ የሰነድ፣ የኦዲዮና ቪዲዮ ማስረጃዎች እንደ ክሱ የሚያስረዱ ሆነው አልተገኙም፡፡ ወይም ምንም ዓይነት ቅርርብ የላቸውም፡፡ በመሆኑም መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ብይን ሰጥቷል፡፡
ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ ግን ለፖሊስ በሰጠው የተከሳሽነት ቃል፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት (ኢሕአዴግ) በምርጫ ወይም በሰላማዊ ትግል የሚወገድ ስላልሆነ፣ በሁከትና በሕዝባዊ አመፅ መወገድ አለበት፡፡ አምኜ እንደ ግብፅ ሁከትና ብጥብጥ በኢትዮጵያም እንዲከሰት ቀስቃሽ ጽሑፎችን ጽፌያለሁ፤›› ብሎ የእምነት ቃል መስጠቱን ፍርድ ቤቱ በንባብ አሰምቷል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በተከሳሹ ላይ የሚያስረዱ ከኢንተርኔት ያቀረባቸው ጽሑፎችም፣ ተከሳሹ ለፖሊስ ከሰጠው ቃል ጋር ተያያዥነት እንዳላቸውና የሚደግፉ መሆናቸውን በመግለጽ እንዲከላከል ብይን ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ብይን ከሰማ በኋላ የተከሳሾች ጠበቃ አቶ አመሐ መኮንን ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ፣ ተከላከል የተባለው ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ ይከላከል የተባለበት የሕግ አንቀጽ ዋስትና ስለማይከለክለው፣ አቅሙን ያገናዘበ ዋስ እንዲፈቀድለት ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም በዋስትና ጉዳይ ላይ ተወያይቶ ለማሳወቅ ለጥቅምት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በብይኑ ላይ ይግባኝ ስለማለቱ ተጠይቆ ፍርድ ቤቱ የሰጠው ብይን እርስ በርሱ እንደሚጋጭ በመጠቆምና የተሰጠው ብይን የቀረበውን ማስረጃ ያላገናዘበና በአግባቡ ያልተመዘነ መሆኑን በመግለጽ፣ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለቱን አስታውቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ብይን በሚመለከት አስተያየታቸውን የሰጡት ጠበቃ አመሐ መኮንን ‹‹ብይኑ ከግለሰብ ችሎታ አንፃር ከታየ በበለጠ በተሻለ ሁኔታ መተንተን ይቻል ነበር፡፡ ከፍርድ ቤቱ አቅም አንፃር ግን ብይኑ ሚዛናዊ ነው፡፡ መረጃዎቹን ከሕጉ ጋር በደንብ አገናዝበው ሠርተውታል፡፡ በአጠቃላይ ጥሩ ብይን ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ሥጋት እንዳላቸው የተናገሩት አቶ አመሐ፣ ሥጋታቸው ደግሞ ፍርድ ቤቱ በነፃ እንዲሰናበቱ የሰጠውን ትዕዛዝ፣ ቀደም ብሎ በሌሎች ደንበኞቻቸው (እነ ሀብታሙ አያሌው) ላይ የተፈጸመው ዓይነት ድርጊት ይፈጸማል የሚለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በዕለቱ እንዲፈቱ ካዘዘ በኋላ፣ የማረሚያ ቤት ኦፊሰር የማስፈቻ ትዕዛዝ ወስዶ ለሚመለከታት የማረሚያ ቤቱ ሠራተኛ መስጠቱን መረጃ እንዳላቸው የተናገሩት አቶ አመሐ፣ የማረሚያ ቤቱ ሠራተኛ በተደጋጋሚ ስትጠየቅ ‹‹አልደረሰኝም›› ማለቷንም መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም በፍርድ ቤት የተገኘውን መብት እንደገና የሚነፈግበት ወይም ሊነጠቅ የሚችልበት ዕድል ሊኖር እንደማይገባም አቶ አመሐ አስረድተዋል፡፡ ከአራትና ከአምስት ለማይበልጡ ጉዳዮች የፍትሕ ሥርዓቱን በጠረባ እየመቱ መጣል ለማንም እንደማይጠቅምም አክለዋል፡፡ ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ጥቅምት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ሌሊት ድረስ ጦማሪያኑ አለመፈታታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ምንጭ ሪፖርተር