ኃይለ ገብርኤል ብሩክ መስከረም ከባተ በኋላ ከሚመጣው የመስቀል ደመራ ጋር ልዩ ትዝታ አለው፡፡ ‹‹ኢዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ፤ መስከረም ሲጠባ ወደ አዲስ አበባ›› እየተባለ የሚዘመርበት ጊዜን፣ በተለይ መስከረም 16 ቀን
በቀዳማዊው ኃይለ ሥላሴ ዘመን በመስቀል አደባባይ ሲከበር የነበረውን ልዩ ልዩ ሥነ ሥርዓቶች ያስታውሳል፡፡ አከባበሩ እንደዘመነ ደርግ በ‹‹አብዮት አደባባይ›› ወይም በዚህኛው ዘመን በመስቀል አደባባይ ብቻ የተወሰነና የታጠረ አልነበረም፡፡
በወቅቱ ደመራው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ከተባረከና ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከለኮሱት በኋላ ከመንፈሳዊው ሥነ ሥርዓት ጎን ለጎን በሥነ በዓሉ ላይ የተገኙት ከከተማዋ የተለያየ ኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ የሰልፍ ትርዒት የሚያሳዩበት ነበር፡፡ የክብር ዘበኛ፣ የጦርና የፖሊስ ሠራዊት በችቦ የታጀበ የሰልፍ ትርዒት ሲያሳዩ፣ መኩሪያ የተሰኘው የንጉሠ ነገሥቱ አንበሳ የተቀመጠበት ሰረገላ ደግሞ በፊት መሪነት በንጉሠ ነገሥቱ ፊት እያለፈ ይጓዝ ነበር፡፡ በዳግማዊ ምኒልክ ጎዳና እስከ ስድስት ኪሎ ድረስ ግራና ቀኝና በየጥጋ ጥጉ ቆሞ የሚመለከተውን የበዓሉ ተሳታፊንም ሰላምታ እየሰጡ ያልፋሉ፡፡
በተለይ ከ50 ዓመት በፊት ከየመንግሥት መሥሪያ ቤቱ የተውጣጡ ከተሜዎች የሚንቦለቦል ችቦ ይዘው ይሰለፉ የነበሩት ሁሉም እጀ ጠባብ የባህል ልብስ ለብሰው ነበር፡፡ ታዳጊ ወጣቶችም ነጭ ሸሚዝና ነጭ ቁምጣ ሱሪ አድርገው በምድር ጦር ማርሽ ታጅበው ስለመስቀሉ ክብር እየዘመሩ ከጦር ኃይሎች ወደ መስቀል አደባባይ ያመሩ እንደነበር ኃይለ ገብርኤል ያስታውሳል፡፡
በአራተኛው ምእት ዓመት፣ በንግሥት እሌኒ አማካይነት ክርስቶስ ኢየሱስ የተሰቀለበት መስቀል መገኘቱ የሚታሰብበት የመስቀል ደመራ በዓል፣ በኢትዮጵያ ለሁለት ሺሕ ግድም ዓመታት ሲከበር ኖሯል፡፡ የበዓሉን ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ትውፊታዊ ገጽታ የተመለከተው ዓለም አቀፉ የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ አድርጎ ከመዘገበው ሁለት ዓመት ሆኖታል፡፡
ክብረ በዓሉ በአማራና በትግራይ ‹‹መስቀል›› ሲባል፣ በተለያዩ ብሔረሰቦች እንደየአካባቢው ቋንቋ የተለያየ መጠርያ አለው፡፡ ለምሳሌ በኦሮሞ ‹‹ጉባ›› ወይም ‹‹መስቀላ››፣ በሀድያ፣ በወላይታ፣ በዳውሮ፣ በጋሞ፣ በጎፋ ‹‹መስቀላ››፣ በከምባታ ‹‹መሳላ››፣ በየም ‹‹ሔቦ››፣ በጉራጌ ‹‹መስቀር››፣ በካፊቾና ሻኪቾ ‹‹መሽቀሮ›› ይባላል፡፡
ምንነቱ
የመስቀል ክብረ በዓል በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበር ብሔራዊ በዓል ነው፡፡ የመስቀል በዓል አጀማመር የክርስትና እምነት መሠረት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል፣ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከተቀበረበት ተቆፍሮ መገኘትና በተለይም የመስቀሉ አንድ ክንፍ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በግሸን ዐምባ መቀመጥ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ቁርኝት ቢኖረውም፣ እያንዳንዱ ብሔረሰብ በዓሉን የሚያከብርበት እንደባህሉ፣ አኗኗሩ፣ ወጉ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ገጽታው የራሱ መንገድ አለው፡፡
የመስቀል በዓል መለያው ደመራው ነው፡፡ ደመራ ንግሥት እሌኒ፣ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት በኢየሩሳሌም ቀራንዮ በሚባል አካባቢ በጎልጎታ ቁፋሮ ያስጀመረችበትን ቀን ለማሰብ የሚከበር ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ የደመራ ሥነ ሥርዓቱ በመጠኑም ቢሆን ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ በአክሱም፣ በዓዲግራት፣ በላስታ፣ ላሊበላ፣ በዋግ ሕምራ፣ በከፊል ጎጃምና በአዊ ዞን ደመራው መስከረም 16 ቀን ቢደመርም ሥርዓተ ጸሎቱ የሚካሄደውና ደመራው የሚለኮሰው መስከረም 17 ቀን ንጋት ላይ ነው፡፡ በአንፃሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በሸዋና በከፊል ጎጃም፣ በሐዲያ፣ በጉራጌ፣ በሸከቾ፣ ካፊቾ፣ ኮንታ ደመራው የሚበራው በዋዜማው መስከረም 16 ቀን ምሽት ነው፡፡ የደመራው አደማመርና አበራር ሥነ ሥርዓት ግን በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው፡፡
የመስቀል ደመራ በዓል በብሔራዊ ደረጃ የሚከበረው በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ ሲሆን፣ እዚህ ደመራ የሚደመረውና ሥርዓተ ጸሎት ተደርጎ የሚቀጣጠለው መስከረም 16 ቀን ወደ ማታ ነው፡፡ በዚሁ በዓል ላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአገር ውስጥና የውጭ ታዳሚዎች ይገኙበታል፡፡ ዘንድሮ በተለይ የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ፖፕ ቴዎድሮስ ዳግማዊ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ባደረጉላቸው ግብዣ መሠረት በክብረ በዓሉ ይገኛሉ፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ባንድ የሰልፍ ትርዒትና በዘመናዊ መሣሪያ በመታገዝ ልዩ ልዩ ጣዕመ ዝማሬን ያሰማል፡፡ ሠረገላ ይነዳል (ይጐተታል)፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ወርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ በዓሉን በተመለከተ ትምህርትና ቡራኬ ከሰጡ በኋላ ደመራውን ባርከው ችቦ በእሳት በማያያዝ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከሚገኙ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ጋር በመሆን ደመራውን ይለኩሳሉ፡፡
ደመራው ወደ አመድነት እስኪለወጥ ይነዳል፡፡ በዚሁ ወቅት ሕዝቡ ‹‹ኢዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ›› በማለት ይዘፍናል፡፡ ሴቶች እልል ይላሉ፡፡ ደመራው የተጸለየበትና የተባረከ ስለሆነ ሕዝቡ አመዱንና ትርኳሹን እየተሻማ ወደቤቱ ይዞ ይሄዳል፡፡ አንዳንዶቹ በአመዱ ግንባራቸው ላይ የመስቀል ምልክት ያበጃሉ፡፡ አመዱ ለሰውም ሆነ ለከብቶች ፍቱን መድኃኒት ነው የሚል እምነት አለ፡፡ በደመራው ማግስት መስከረም 17 ቀን በሚከበረው ዋናው የመስቀል በዓል ምዕመኑ ቤተ ክርስቲያን አስቀድሶ ከተመለሰ በኋላ ሲበላና ሲጠጣ፣ ከጎረቤትና ዘመድ አዝማድ ሲገባበዝና ሲጠያየቅ በፍቅርና በደስታ በዓሉን ሲያከብር ይውላል፡፡
የምርቃት ሒደት
ክብረ በዓሉን ከሚገልጹት ባህላዊ መገለጫዎች አንዱ ምርቃት ነው፡፡ ለዓይነት የስድስቱን ብሔረሰቦች አመራረቅ ከተለያዩ ምንጮች ያገኘነውን እነሆ፡፡
በሀዲያ
ደመራ የሚቀጣጠለው መስከረም 16 ሲሆን፣ መጀመሪያ በዕድሜ ትልቅ የሆኑ በየመንደሩ ያሉ አዛውንቶች ‹‹እንኳን በሰላም አደረሰን እንኳን በሰላም ብርሃን አየን ከጨለማም ወጣን›› እያሉ በመመረቅ ችቦ ይለኩሳሉ፡፡ ከዚያም ወጣቶች እየተጫወቱ ደመራውን ይዞራሉ፡፡ ሲነጋጋ ከብቶች ደመራውን ይዞራሉ፡፡
በወላይታ
ጨዋታው ሲያበቃ ለመስቀል የታረደውን በሬ እየተመገቡ ይመራረቃሉ፡፡ ‹‹እስከ መጨረሻው እንኖራለን የዳሞታ ተራራ እንደኖረ፣ የኮይሻ ተራራ እንደኖረ እኛም እንኖራለን፡፡ አህያ ቀንድ እስኪያወጣ እንኖራለን፡፡ ኮንድቾ በጣም አጭር እንጨት ምሰሶ እስከሚሆን እንኖራለን፤›› እያሉ መጪውን ዘመን በተስፋ በመቀበል ይለያያሉ፡፡
በሸከቾ
በበዓሉ ቀን ጧፍ በማብራት በየጓዳው በየእህል ማስቀመጫው ይዞ በመግባት ‹‹መጥፎ ነገር ከቤት ውጣ፣ ሀብት ግባ›› እያሉ ከመረቁ በኋላ ጎረቤት ተጠራርቶና ተሰባስቦ ችቦ ይበራል፡፡ በነጋታው የእርድ ሥርዓት የሚከናወን ሲሆን ቤተሰብና ጎረቤት በመስቀል ይጠራራል ይገባበዛል፡፡
በየም
በዋዜማው ሌሊት ሊነጋ አቅራቢያ ‹‹የረሀብ ምንቸት ውጣ ጥጋብ ግባ›› በማለት ችቦ ከተለኮሰ በኋላ ወደ ደመራው ቦታ ሁሉም ያመራል፡፡ ደመራው በአዛውንቶች ተመርቆ ይለኮሳል፡፡
በካፍቾ
የደመራ በዓሉም የሚከበረው በባህላዊ እምነት መሪው ግቢ ውስጥ ሲሆን እያንዳንዱ ሰው ችቦ በየቤቱ ለኩሶ በራሱ ቤት ዙሪያ በመዞር ድህነት ውጣ፣ ሀብት ግባ ብሎ መልካም ምኞቱን ከገለጸ በኋላ የተቀጣጠለውን ችቦ የባህላዊ እምነት መሪው ግቢ በተዘጋጀው ደመራ ላይ ወስዶ ይለኩሳል፡፡ በማግስቱ ሠንጋ ይታረድና የደመራው እሳት በነደደበት ቦታ ላይ እሳቱን ለማቀዝቀዝ ሲባል ደም ይፈስበታል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ደሙን በእጁ በመንካትና ከአመድ ጋር በመለወስ ግንባሩ ላይ ይቀባል፡፡
በጎፋ
ማስቃላ ዮ! ዮ! እያሉ የተለያዩ የበረከት ሀሳቦችን ይለዋወጣሉ (መስቀል እንኳን መጣህልን) ማለት ነው፡፡ አስከትለውም እየደጋገሙ ማስቃላ ዮ! ዮ! ዳናው ዳና አልባ ዙማዳን ዳና (አልባ ዙማ በአካባቢው የሚገኘው ትልቅ ተራራ ሲሆን እንደሱ እንኖራለን እንደ ማለት ነው፡፡) ክንቲ ሻላዳን ዳና (ክንቲ ሻላ ማለት በአካባቢው የሚገኘው ትልቁ አለት ሲሆን እንደሱ እንኖራለን እንደ ማለት ነው፡፡) መሪናው ዳና (ለዘለዓለም እንኖራለን) ማለት ነው፡፡ ሀረይ ካጨ ከሳናዳን (አህያ ቀንድ እስከሚያበቅል ድረስ እንኖራለን፡፡) ገላኦ ገል ውራናስ ዳና (ሁሉም ልጃገረዶች እስኪያገቡ ድረስ እንኖራለን)፡፡ እንዲህ እያሉ እርስ በርስ ይሸካከማሉ ይተቃቀፋሉም፡፡
የመስቀል በዓል በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች፣ በገጠርም በከተማም፣ በደብርም በገዳምም እንደ ኅብረተሰቡ ባህልና ልማድ በታላቅ አክብሮት በየዓመቱ ይከበራል፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ ብሔረሰቦች እንደ ካፊቾ፣ ወላይታ፣ ሸክቾ፣ ኮንታ ያሉት እንደዘመን መለወጫ ይቆጥሩታል፡፡ በተለይ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በሸከቾ በመሽቀሬ ባሮ በዓል ላይ ደመራ ነዶ ሲያበቃ አስራ ሁለት ጉማጅ እንጨቶችን ከውስጡ በመልቀም ስልቻ ውስጥ ያስቀምጡና አንድ ወር ባለፈ ቁጥር አንድ ጉማጅ እየተጣለ ከአሥራ ሁለት ላይ ሁለት ጉማጆች ብቻ ሲቀሩ የዘመን መለወጫ በዓል እየደረሰ መሆኑንና ድግሱ ከወዲሁ መጀመር እንዳለበት ኅብረተሰቡን ያሳስቡታል፡፡
የኢትዮጵያውያን የመስቀል በዓል አከባበር ከተቀረው የዓለም ክፍል የተለየ፣ ወቅቱም ክረምቱ አልፎ የበጋ በመሆኑ በዓሉ ካለው ሃይማኖታዊ ፋይዳ ባሻገር በርካታ ማኅበራዊ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይጠቀሳል፡፡
መስቀል በዓልን ባለም ቅርስነት ባስመዘገበው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን መረጃ መሠረት፣ ዓመቱን በሙሉ ተለያይተው የኖሩ የቤተሰብ አባላትና ዘመዳሞች የሚገናኙበትና የሚጠያየቁበት፣ ማኅበራዊ ችግሮቻቸውን የሚፈቱበትና የሚረዳዱበት፣ ወጣቶች የሚተጫጩበትና ራሳቸውን ለጋብቻ የሚያዘጋጁበት፣ በጋብቻ የተሳሰሩ ቤተሰቦች የሚጠያየቁበት፣ የተጣሉ ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና በጥል የተለያዩ ባልና ሚስቶች ባጠቃላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በመፍታት እርቅ የሚወርድበትና ሰላም የሚሰፍንበት ነው፡፡
መስቀል፣ በማኅበረሰቡ አባላት መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር የጎላ ድርሻ የሚያበረክት፣ እንደ ቤተሰብና አካባቢው በአዲሱ ዓመት የሚሠሩ ሥራዎች ተለይተው እንዴት መሠራት እንዳለባቸው የሚመከርበትና የሚታቀድበት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች እዳ የሚሰረዝበትም ነው፡፡
ወጣቶች በአባቶች የሚመረቁበት፣ ጎልማሶች ዕውቀትን ከአባቶች የሚቀስሙበት፣ ኃላፊነት የሚረከቡበት፣ ለኢትዮጵያ ሠላምና ብልጽግናን በመመኘት ጸሎት የሚደረግበት፣ ሕዝቡ የሚዘፍንበት፣ የሚጨፍርበት፣ የሚደሰትበት፣ ግጥም የሚገጥምበት ድምፁን የሚያሟሽበት፣ ወጣቱ የሚኮራበት፣ ባህሉን የሚያጠናበት፣ የሚለወጥበት ወቅትና በአጠቃላይም ቤተ ክርስቲያን ለበዓሉ ከምትሰጠው ሃይማኖታዊ ትርጉምና ሥርዓት በመነሣት በበርካታ ብሔረሰቦች ዘንድ ጥልቅ የሆነ የመተሳሰብ፣ የፍቅር፣ የወዳጅነት መንፈስ የሚጎለብትበት ወቅት መሆኑ ከፋይዳው ይጠቀሳሉ፡፡
በዓሉን በተመለከተ በኢንቬንተሪም ሆነ በጥናትና ምርምር የተገኙ ዕውቀቶችንና ልምዶችን በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ማካተት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና አዋቂዎች ስለመስቀል በዓል ቅርስ ምንነትና ጠቀሜታ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለወጣቶች ማስተዋወቅ እንዲችሉ ማመቻቸት ለቅርሱ ቀጣይነት እየተደረጉ ያሉ እንክብካቤዎች መሆናቸውን ባለሥልጣኑ አመልክቷል፡፡
ምንጭ ሪፖርተር ተጻፈ በ ሔኖክ ያሬድ