በቅርቡ ይፋ በተደረገው የአዲስ አበባ ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምደባ ሸራተን አዲስ፣ ኢሊሊ ዓለም አቀፍ ሆቴልና ካፒታል ሆቴልና ስፓ፤ 5 ኮከብ የተሰጣቸው ሲሆን ሸራተን አዲስን ጨምሮ 20 ሆቴሎች በኮከብ አሰጣጡ ላይ ቅሬታ አቅርበው ምላሽ እየተጣበበቁ ነው፡፡
ባለ 5 ኮከብ ደረጃ ይሰጣቸዋል ተብሎ የተጠበቁት ሂልተን አዲስና ራዲሰን ብሉ ሆቴል ባለ 4 ኮከብ ሆነዋል፡፡
5 ኮከብ የተቀዳጁት ኢሊሊ እና ካፒታል ሆቴል በተሰጣቸው ደረጃ ደስተኛ መሆናቸውን የገለፁ ሲሆን ሸራተን አዲስ ግን ከ5 ኮከብ በላይ ይገባኛል የሚል ጥያቄ አቅርቧል፡፡
ካፒታል ሆቴል 12 በሚደርሱ መስፈርቶች መመዘኑን የጠቆሙት የሆቴሉ ሴልስና ማርኬቲንግ ማናጀር አቶ ሚካኤል ተካ፤ ከመቶ 85.68 በማግኘትም ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ለመሆን መብቃቱን ገልፀዋል፡፡ ሆቴላችን የ5 ኮከብ ባለቤት መሆኑ በአለማቀፍ ደረጃ ያለው ተቀባይነት እንዲጨምርና ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲዘልቅ ይረዳዋል ያሉት ማናጀሩ፤ ሆቴሉ ወደፊት ሊጀምር ያቀዳቸው ሌሎች አገልግሎቶች ሲሟሉ፣ ወደ “ግራንድ ሌግዠሪ” ደረጃ ማደግ እንደሚችል መዛኞቹ መጠቆማቸውን ተናግረዋል፡፡
ሆቴላቸው 5 ኮከብ ማግኘቱ እንዳስደሰታቸው የተናገሩት የኢሊሊ ዓለም አቀፍ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር አብዱሰላም ባሬንቶ በበኩላቸው፤ የተሰጠው ደረጃ ሆቴሉ በእንግዶች ዘንድ ይበልጥ ተመራጭ እንዲሆን እንደሚረዳና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለማቅረብ እንደሚያተጋቸው ገልፀዋል፡፡ የሸራተን አዲስ ሆቴል አንድ የስራ ሃላፊ በስልክ በሰጡን አስተያየት፤ ሆቴሉ በኮከብ ደረጃ አሰጣጡ ላይ ያሉትን ቅሬታዎች ለሚመለከታቸው አካላት አቅርቦ ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው ጉዳዩ፣ እልባት ሲያገኝ ውጤቱ ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የባህልና ቱሪዝም የህዝብ አለማቀፍ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ገዛኸኝ አባተ በበኩላቸው፤ በኮከብ ደረጃ ምደባው ላይ 20 ሆቴሎች ቅሬታ ማቅረባቸውን ጠቁመው፤ ቅሬታቸው ምላሽ ማግኘቱንና በሚቀጥለው ሳምንት ይፋ እንደሚደረግ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ ሆቴሎች 95 ያህሉ ለምዘና ተመርጠው የነበረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ፣ 38ቱ ከ 1 ኮከብ እስከ 5 ኮከብ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት፤ ከ5 ኮከብ በላይ “ግራንድ ሌግዠሪ” ያገኘ ሆቴል የለም፡፡ የኮከብ ደረጃ ከተሰጣቸው መካከልም 3ቱ ባለ 5 ኮከብ 11ዱ ባለ 4፣ 13ቱ ባለ 3፣ 10ሩ ባለ 2 ኮከብ ደረጃ ሲያገኙ አንድ ሆቴል ባለ 1 ኮከብ ደረጃ ተሰጥቶታል፡፡ ለሁሉም ሆቴሎች ተመሳሳይ 12 የመመዘኛ ነጥቦች የተዘጋጁ ሲሆን ባገኙት የመቶኛ ውጤት መሠረት ደረጃው ተሰጥቷቸዋል ተብሏል፡፡ የሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምዘናው ከተጀመረ 5 ወራት ገደማ ያስቆጠረ ሲሆን በአሁን ወቅት በክልል ከተሞች ለሚገኙ ሆቴሎች ተመሳሳይ የምዘና ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የሆቴል ምዘናው የሚከናወነው በተባበሩት መንግስታት የአለም ቱሪዝም ድርጅት ሲሆን ለስራው የሚውለው በጀት የተገኘው ከአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) እንደሆነም ታውቋል፡
ምንጭ፦ አዲስ አድማስ
↧
ሸራተን አዲስ ከ5 ኮከብ በላይ ይገባኛል ሲል ቅሬታ አቀረበ
↧