የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፻፲፰ኛ ፖፕ እና የመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎድሮስ ካልዕ፣ በመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ላይ ለመታደም እና የአራት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ፣ መስከረም ፲፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም. ከቤተ ክርስቲያኒቱ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋር በመኾን አዲስ አበባ ይገባሉ፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎድሮስ ካልዕ የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የእስክንድርያ ፻፲፰ኛ ፖፕ እና ፓትርያርክ ዘመንበረ ማርቆስ
ፓትርያርክ አቡነ ቴዎድሮስ አራት ቀናት በሚወስደው ቆይታቸው፣ መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም. በሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ ከመታደማቸው በተጨማሪ፣ ወደ አኵስም እና ላሊበላ አቅንተው ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ሥፍራዎችን እንደሚጎበኙም ታውቋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በሚኖራቸው ቆይታ፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላትን፣ እንዲኹም ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ከታዋቂ ግለሰቦች ጋር እንደሚነጋገሩ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ጉዟቸውን አስመልክቶ ቅዱስነታቸው ከሳምንት በፊት ከግብጽ የውኃ ሀብት ሚኒስትር ሆሳም አል ሞጋሃዚ ጋር መነጋገራቸው የተዘገበ ሲኾን፣ በውይይታቸውም ወቅት ግብጽ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ ያላትን ጥያቄዎች አንሥተው ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ጋር ውይይት እንዲያደርጉ ሚኒስትሩ መጠየቃቸውና የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ተዘግቧል፡፡
ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስ በበኩላቸው ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት ባላቸው ታሪካዊ ግንኙነት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እየተባበሯቸው እንደኾነና አስተዋፅኦዋቸውም ከፍተኛ እንደኾነ ገልጸዋል፤ በማለት ስታር አፍሪካ በተሰኘ ድረ ገጽ ላይ የወጣ ዘገባ ያትታል፡፡
የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ግብጽን ለስድስት ቀናት በይፋ በጎበኙበትና በካይሮ ፕሬዝዳንታዊ ቤተ መንግሥት ከፕሬዚዳንት አልሲሲ ጋር በተወያዩበት ወቅት ፕሬዚዳንቱ፣ የዓባይ ወንዝ ለኢትዮጵያውያን የልማት ምንጭ ቢኾንም ለግብጽ ግን ልማት ብቻ ሳይኾን የደም ሥር መኾኑንም መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስም በበኩላቸው፣ በጠንካራ ትስስር ላይ ለተመሠረተው የኹለቱ አገሮች ግንኙነት፣ ከዓባይ የሚመነጭ ውኃ የማያቋርጥ የጋራ ሀብት በመኾኑ በፍትሐዊነትና በእኩልነት ተጠቃሚ የሚኮንበት ይኾናል ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡
ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስ ካልዕ፣ እ.ኤ.አ. በ፲፱፻፶፪ ማንሱራ በተሰኘ የግብጽ ከተማ የተወለዱ ሲኾን፣ በ፲፱፻፸፭ ከኤሌክሳንደርያ ዩኒቨርሲቲ በፋርማሲ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ ለጥቂት ዓመታት በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚገኝ መድኃኒት ፋብሪካን ከአስተዳደሩ በኋላ፣ ቅዱስ ፒስሆግ የተባለ ገዳም ገብተው የሥነ መለኰት ትምህርት በማጥናት እ.ኤ.አ. በ፲፱፻፹፱ ተመርቀዋል፡፡
ከሦስት ዓመት በፊት ያረፉትን የቀድሞውን ፓትርያርክ አቡነ ሺኖዳን በመተካት በአኹኑ ወቅት ፻፲፰ኛው የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፖፕ እና የመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ በመኾን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን ታሪካዊው የቅዱስነታቸው ጉብኝት የተሳካ ይኾን ዘንድ፣ በፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የሚመራ ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሚቴ በማቋቋም ዝግጅት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡
ምንጭ ሐራ ዘተዋሕዶ