በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማት እና አድባራት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ተጠቃሚ በማያደርጉ የመሬት እና የገቢ ማስገኛ ተቋማት የኪራይ ውሎች፣ የተጧጧፈ ዘረፋ እና ምዝበራ መፈጸሙን በጥናት ያረጋገጠው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት÷ በጥምርና በተናጠል በሕግ ተጠያቂ የሚኾኑ የሥራ ሓላፊዎች እና ሠራተኞች በስም ዝርዝር ተለይተው እንዲቀርቡለት ለአጥኚ ኮሚቴው ትእዛዝ ሰጠ፤ በመሬት፣ በሕንጻዎች፣ በሱቆች፣ በመቃብር ቦታዎች፣ በመኪና ሽልማት እና በመሳሰሉት የልማት ሥራዎች ዙሪያ በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው ስለሚገቡ ነጥቦች፣ ለሀገረ ስብከቱ ጥብቅ መመሪያም አስተላልፏል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ የሥራ አስፈጻሚ እና የአስተዳደር አካል የኾነው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ መመሪያውንና ትእዛዙን የሰጠው÷ የሀገረ ስብከቱን 48 ገዳማት እና አድባራት ያካተተውን የመሬት፣ የሕንጻዎችና የገቢ ማስገኛ ተቋማት የኪራይ ተመንና የመኪና ሽልማት ጉዳዮች ጥናታዊ ሪፖርት ቋሚ ሲኖዶሱ ተቀብሎ ያሳለፈውን ውሳኔ መሠረት በማድረግ ነው፡፡
ቋሚ ሲኖዶሱ፣ ነሐሴ ፳፰ እና ፳፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ባካሔዳቸው ስብሰባዎች፣ አጥኚ ኮሚቴው በ33 ገጾች በማካተት በአንድ ጥራዝ ካቀረባቸው 48 አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ÷ 15ቱ በከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኙ፤ ኹለቱ በመካከለኛ ደረጃ የተቀሩት ስድስቱ ደግሞ በደኅና ኹኔታ ላይ እንዳሉ ተገንዝቧል፡፡
ከፍተኛ ችግር ያለባቸው 15ቱ አብያተ ክርስቲያናት÷ የቦሌ ቡልቡላ መድኃኔዓለም፣ የቦሌ ገርጂ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ቅዱስ ገብርኤል፣ የጃቲ መካነ ሕይወት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት፣ የደብረ ኢዮር ቅዱስ ሚካኤል፣ የመካኒሳ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል፣ የደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ፣ የመካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ፣ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የጽርሐ አርያም ቅዱስ ሩፋኤል፣ የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል፣ የምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤል፣ የሰሚት ኆኅተ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት፣ የደብረ ገሊላ ቅዱስ ዐማኑኤል ካቴድራል፣ የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም፣ የብሔረ ጽጌ ቅድስት ማርያም፣ የደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል እና የየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል እንደኾኑ በውሳኔ ቃለ ጉባኤው ተዘርዝረዋል፡፡
በተዘረዘሩት ገዳማት እና አድባራት፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ መገልገያ ከመንግሥት የተሰጡ መሬቶች እና በይዞታዎቹ ላይ ለገቢ ማስገኛ በሚል የተሠሩ ሕንጻዎች እና ሱቆች፣ የ“ልማት አርበኛ” እየተባሉ በካህናቱ እና ምእመናኑ ስም የሚሸለሙ ሓላፊዎች እና ሠራተኞች ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ለምዝበራ እንዳጋለጧቸውና አላግባብ ሀብት እንዳፈሩባቸው በጥናቱ ሒደት በማስረጃ በመረጋገጡ ጉዳያቸው በሕግ አግባብ እየታየ ክሥ እንዲመሠረትባቸው በጠቅላይ ጽ/ቤቱ አስተዳደር ጉባኤ ቀደም ሲል ተወስኗል፡፡
የጠቅላይ ጽ/ቤቱን ውሳኔ የተቀበለው ቋሚ ሲኖዶሱ፣ ለሕጋዊ ጥያቄ እና አካሔድ አመቺነት መሟላት ይገባቸዋል ያላቸውን ነጥቦች በመለየት ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ በዝርዝር አስታውቋል፡፡
በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት፣ በጥምር እና በተናጠል በሕግ ተጠያቂ የሚኾኑ የሥራ ሓላፊዎች እና ሠራተኞች ስም ዝርዝር ከተሰበሰቡት ማስረጃዎች ጋር እየተነጻጸረ በሰነድ ተደግፎ እንዲቀርብለት ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ለአጥኚ ኮሚቴው ጳጉሜን ፲፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. አስቸኳይ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
በተጨማሪም፣ በተጠቀሱት ገዳማት እና አድባራት የአካባቢ የመሬት ዋጋ በካሬ ሜትር ስንት እንደኾነ፣ የተሰጠው የኪራይ ውል ዓመት ከስንት እስከ ስንት ዓመት እንደኾነ በአሐዝ እንዲገለጽ፣ የቤት እና የመኪና ሽልማት የተሰጣቸው አለቆች እና የስጦታው ምክንያት ተብራርቶ እንዲቀርብ፤ በአጠቃላይ በጥናቱ ሒደት የተሰበሰቡት 1500 ማስረጃዎች ለሕጋዊ ጥያቄ አመቺ በሚኾንበት አኳኋን በሚገባ ተጣርተው እንዲዘጋጁ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ አጥኚ ኮሚቴውን አዟል፡፡
ገዳማቱንና አድባራቱን በበላይነት በሚቆጣጠረው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም፤ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያንን የመሬት አጠቃቀም እና የገቢ ማስገኛ ተቋማት አጠቃቀምበተመለከተ ትኩረት ሊሰጣቸውና በአግባቡ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚገባቸው ነጥቦች በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ የተመለከቱ ሲኾኑ፤ ጠቅላይ ጽ/ቤቱም በውሳኔዎቹ ላይ በመመርኮዝ ለሀገረ ስብከቱ በጻፈው ደብዳቤ ጥብቅ መመሪያ ሰጥቶባቸዋል፡፡
በዚኽም መሠረት፣ በገዳማቱ እና በአድባራቱ የመሬት እና የሱቅ እንዲኹም የልማት ይዞታዎች የኪራይ ውላቸው ለአንድ ዓመት ብቻ ይኾናል፤ የተለየ ችግር ካጋጠመም ውሉ በሕግ እንዲቋረጥ ታዟል፡፡
የመቃብር ቦታዎች አጠቃቀም፤ የቦታዎች እና የሱቆች ኪራይ አፈጻጸም በአጠቃላይ የልማት ነክ ጉዳዮች ኮሚቴ ተቋቁሞ እና ውስጠ ደንብ ወጥቶላቸው እንዲሠሩ፤ ውሎቻቸውም በየደረጃው ተጠንተው ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቀርበው ተቀባይነት ካገኙ በኋላ ተግባራዊ እንዲኾኑ ተወስኗል፡፡
የቤት እና የመኪና ሽልማት በቢሮ ደረጃ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቀርቦ ሳይታይና በቋሚ ሲኖዶስ ሳይጸድቅ እንዳይፈጸም ታዟል፡፡ ከሦስተኛ ወገን ጋር ቤተ ክርስቲያኒቱ መዋዋል እንደምትችል የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ቋሚ ሲኖዶሱ አጽድቋል፤ የመንበረ ፓትርያርክ የሕግ አገልግሎትም፣ ውሎች ወጥ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን መብቶች የሚያስከብሩና የሚያስቀድሙ መኾናቸውን በማረጋገጥ ውሳኔውን ለውጤት እንዲያበቃ በቋሚ ሲኖዶሱ ተወስኗል፡፡
በመሬት፣ በሕንጻዎች፣ በሱቆች እና በመሰል የገቢ ማስገኛ ተቋማት ዙሪያ በተጨባጭ ጥናት እንደተረጋገጠው ኹሉ ቤተ ክርስቲያናችን በእጅጉ ተጎጂ እና የበይ ተመልካች የኾነችበት ኹኔታ በመፈጠሩ የሚከተሉት የመፍትሔ ሐሳቦች ቀርበዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱን በማይጠቅሙና ለግለሰብ ነጋዴዎች በሚያመዝኑ መልኩ የተገቡ ውሎች በሙሉ ለአንድ ወገን ጥቅም የሚያመዝኑ መኾናቸው እየተገለጸ እንዲፈርሱና በሌላ ውል እንዲተኩ እንዲደረግ በማድረግ አዲስ ውል በመዋዋል የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥቅም ማረጋገጥ፡፡
በጥናቱ ወቅት እንደተመለከትነው÷ የአንዱ ደብር ውል አንድ ዓመት፣ የሌላኛው 10 ዓመት እንዲኾን ስለተደረገና አንዳንድ ውሎችም የቤተ ክርስቲያኒቱን ሳይኾን የተከራዮችን መብት የሚያስከብሩ ኾነው በመገኘታቸው ውሎቹ ወጥ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥቅም የሚያስከብሩ መኾን ይገባቸዋል፡፡ ስለኾነም በሕግ ዐዋቂዎች የሚዘጋጅና ወጥነት ያለው ውል በማእከል ደረጃ እንዲዘጋጅ በማድረግ ኹሉም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አንድ ወጥ በኾነ ውል የሚሠሩበትን ኹኔታ ማመቻቸት፡፡
በቃለ ዐዋዲው አንቀጽ ፲፪ ንኡስ አንቀጽ ፰ መሠረት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የጨረታውን ሒደት ተመልክተው ሲያጸድቁት እንዲፈጸም በማድረግ ሥራዎችን በሕግና በሥርዐት ማከናወን፡፡
ማንኛውም ዐይነት የሽልማት ሥነ ሥርዐት መኪናን ጨምሮ የሥራ አፈጻጸም ተገምግሞ በሀገረ ስብከቱ በኩል ታምኖበት በሊቀ ጳጳሱ እና በቅዱስ ፓትርያርኩ ሲፈቀድ ከሚፈጸም በስተቀር ምንም ዐይነት ሽልማት እንዳይከናወን ማድረግ፡፡
በየአድባራቱ በሰንበቴ ማኅበራት ስም የሚሠሩ የመካነ መቃብር ፉካዎች የሕዝበ ክርስቲያኑን በቤተ ክርስቲያን እኩል አገልግሎት የማግኘት መብት የሚገድቡ በመኾኑ አዳዲስ የሰንበቴ ማኅበራት ፉካዎችን እንዳይገነቡ ማድረግ፡፡
የመሬት እና የቦታ ኪራይ ጥያቄን ለማስተናገድ፡-
አጥቢያዎች መሬትም ኾነ ሱቅ በሚያከራዩበት ወቅት የየክፍለ ከተማቸውን የመንግሥት የሊዝ ኪራይ ዋጋን ባገናዘበና የየአካባቢያቸውን የንግድ ማእከላት የገበያ ኹኔታ መሠረት ባደረገ አግባብ ቤተ ክርስቲያንን ተጠቃሚ ሊያደርግ ይቻል ዘንድ፣ ጨረታውን በግልጽ እንዲያካሒዱ በሀገረ ስብከቱ በኩል ጥብቅ መመሪያ እንዲሰጣቸው ማድረግ፡፡
አድባራቱ መሬትም ይኹን ሱቅ ሲያከራዩ፣ የሚያከራዩትን ቦታ፣ የሚያከራዩትን ሱቅ ብዛት፣ ቦታውን ወይም ሱቁን ለማከራየት የፈለጉበትን ዝርዝር ኹኔታ እና የሚከራዩት ቦታዎችም ኾኑ ሱቆች በገበያው ያላቸው አዋጭነት ተጠንቶ በመዘርዘር ለሀገረ ስብከቱ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ሀገረ ስብከቱም የቀረበለትን የኪራይ ጥያቄ ተገቢና ትክክለኛ መኾኑን በማጥናት በአስተዳደር ጉባኤ ወስኖ እንዲያከራዩ መፍቀድ ወይመው መከልከል ይችላል፡፡
አጥቢያዎች ቦታም ኾነ ሱቅ እንዲከራዩ ሲፈቀድላቸው በግልጽ ጨረታ ያከራያሉ፤ ጨረታውም የሀገረ ስብከት፣ የምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች በተገኙበት መካሔድ ይኖርበታል፡፡
በአጥቢያ እንዲከራይ የተፈቀደው ቦታና ሱቅ በሕጋዊ መልኩ ግልጽ ጨረታ ከተካሔደ በኋላ ውጤቱ ለሀገረ ስብከቱ እንዲደርሰው ይደረጋል፡፡ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ የተከራየው ቦታ ወይም ሱቅ፣ በሕጋዊ መንገድ የአካባቢ ዋጋና የመንግሥት የሊዝ ኪራይ ዋጋ ባማከለ መልኩ በይበልጥም ቤተ ክርስቲያንን ተጠቃሚ በሚያደርግ አግባብ ማከራየታቸውን በአስተዳደር ጉባኤው ካረጋገጠ በኋላ የኪራይ ውሉ እንዲፈጸም ያደርጋል፡፡
በአጥቢያ የሚከራይ መሬት ይኹን ሱቅ የኪራይ ውል የሚሰጠው ለአንድ ዓመት ብቻ ኾኖ ውሉ ወጥና ለቤተ ክርስቲያኒቱ የሚጠቅም በኾነ መልኩ በሕግ ባለሞያዎች ተጠንቶ በሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ከታመነበት በኋላ አድባራቱ በአዲሱ ውል ተከራዮቻቸውን እንዲያዋውሉ ማድረግና የውላቸው ግልባጭ ለሀገረ ስብከቱ እንዲላክ መደረግ ይኖርበታል፡፡
ሀገረ ስብከቱም ቦታዎቹ እና ሱቆቹ በሕጉ መሠረት እየተከራዩ መኾናቸውን በማረጋገጥ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ማሳወቅና ማስፈቀድ ይኖርበታል፡፡
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤትም ሀገረ ስብከቱ በመሬት፣ በሕንጻዎችና በመሰል የገቢ ማስገኛ ተቋማት ዙሪያ ለሚያከናውነው ሕጋዊ የሥራ አፈጻጸም በሙሉ ተገቢውን ድጋፍና ትብብር በማድረግ ለሥራው ውጤታማነት የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅበታል፡፡
ማንኛውም ተከራይ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተከራየውን ሱቅ ወይም ቦታ ለሦስተኛ ወገን ማከራየት አይችልም፡፡ አከራይቶ ቢገኝ ያለምንም ቅድመ ኹኔታ የተከራየውን ሱቅ ወይም መሬት እንዲለቅ ይደረጋል፡፡
ማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዞታ በውል የተከራየ ሰው በተከራየው ባዶ ቦታ ላይ ሱቅ ሠርቶ ወይም ቦታውን ሸንሽኖ ለሦስተኛ ወገን ማከራየት አይችልም፡፡
ማንኛውም የንግድ ቤት ወይም ቦታ ተከራይ የንግድ ስያሜ ለወንድሜ፣ ለእኅቴ፣ ለጓደኛዬ…ወዘተ እንዲዞር ይደረግልኝ የሚል ጥያቄ፣ ከውስጥ ለውስጥ የቁልፍ ወይም የቦታ ሽያጭ ጋር የሚካሔድ በመኾኑ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ /ጥናታዊ ሪፖርት፤ የመፍትሔ ሐሳቦች፤ ከገጽ 31 – 33/
በጥናቱ ያልተካተቱት ገዳማት እና አድባራት ችግር እንደሌሎቹ ተጠንቶ እንዲቀርብም በቋሚ ሲኖዶሱ በተወሰነው መሠረት ጠቅላይ ጽ/ቤቱ መመሪያ በመስጠቱ፣ ጥናቱ በቀሪዎቹ ከመቶ በላይ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ላይም ቀጣይነት እንደሚኖረው ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህም ኾኖ የጥናቱን ሒደቱ እና ፋይዳ በየመድረኩ በማጥላላት እና በማንቋሸሽ የተጠመዱት ቀንደኛ አማሳኞች እና ግብረ አበሮቻቸው የኮሚቴውን አባላት በጎጠኝነት እና በጥቅም ኔትወርክ ለመደለል ከመሞከር ጀምሮ ከስም ማጥፋት፣ ከዛቻ እና ከማስፈራራት ባለፈ የጥቃት ውጥኖች ለማሰናከል እየሞከሩ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡
“አጥፍተናችኹ አገራችን እንገባለን” የሚለው የቀንደኛ እና ልማደኛ አማሳኞች ፉከራ ለጥቃት ውጥኑ በማሳያነት እንደሚጠቀስ ለኮሚቴው አባላት ቅርበት ያላቸው የዜናው ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ሐራ ዘተዋሕዶ