ሰራዊት ፍቅሬና ግብራበሮቹ አይናቸውን በጨው አጥበው መጥተዋል!-ኤፍሬም እውነቱ (አሱ)
ትዝ ይላቹሃል? … የዛሬ አምስት አመት የአዲስ አመት ዋዜማ ላይ ሰራዊት ፍቅሬና ግብራበሮቹ የመጀመሪያውን “የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ” አዋዝተው ሲያበስሩን?
እንደውም አቶ መለስ ሚሊኒየም አዳራሽ ወጣቱ ፊት ቆመው “የሚሰሩ እጆች ይዘን፣ የሚያስብ ጭንቅላት ይዘን፣ የወጣቱን መንፈስ ይዘን … ስንዴ የምንለምንበት ጊዜ መቆም አለበት።” ያሉ ጊዜ? … አዎ አስታውሳችሁታል።
ይሄን የአቶ መለስ ንግግር (ebc ታሪካዊ ይለዋል)
ወጣቱ ግን የተረጎመው በሌላ ይመስለኛል። አቶ መለስ ” … ስንዴ የምንለምንበት ጊዜ መቆም አለበት” ሲሉ ወጣቱ “አዎ የሚያስብ ጭንቅላት ይዘን ሁሌ ስንዴ መለመኑ ይሰለቻል እዛው ዳቦ ያለበት ብንሄድ ይሻላል” ብሎ ያሰበ ይመስለኛል።
ለዛም ነው ባለፉት አምስት አመታት ወጣቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ በሀገሩ ተስፋ ቆርጦ ሞትና ስቃይ ሳያስፈራው እንደ ጉድ እየተሰደደ ያለው።
እንደ አርቲስቶቻችን ዲስኩር
ግን ኢትዮጵያ በ2007 በጉጉት ምራቅ የምታስውጥ፣ ዲቪ የምታስልክ ሀገር ትመስል ነበር። የዛኔ በቴሌቪዥን መስኮት ባቡሩ በዚ ልማቱ በዚ የሚዥጎደጎድባትን የ2007ቷን ኢትዮጵያ ስናይ አያቴ ወደኔ እየተመለከቱ “እድሜ ያለው ይሄን ሁሉ ተዓምር ያያል እኛ እንኳን አብቅቶልናል” አሉ። ምስኪን አያቴ 2007 ሩቅ መስሏቸው!
አያቴ ይሄን ባሉበት አፋቸው ባለፈው በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ዘግናኝ ድርጊት ሲያዩ “ይሄን ጉድ ልታሳየኝ ነው ያስቀመጥከኝ?” አሉ ሳግ እየተናነቃቸው።
ታዲያ ከዚ ሁሉ በኋላ አርቲስቶቻችን አይናቸውን በጨው አጥበው “ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መጀመር እናበስራለን የአዲስ አመት ዋዜማ ላይ እንገናኝ” እያሉን ነው።
ሙሉአለም ታደሰ ትንታግ ሆና “ሻማ ለልደት ብቻ ይበራል!” እንዳለችው ሳይሆን መሃል አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ብለን ዛሬም በመብራት መቆራረጥ አሳራችንን እየበላን አለን።
ዛሬም ስኳርና ዘይት ለመግዛት፣ ታክሲ ለመያዝ … ሰላማዊ ሰልፍ የሚያስንቁ ረዣዥም ሰልፎችን እያስተናገድን አለን።
በርግጥ “የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅዱ” የለወጠው ነገር የለም ማለት አይቻልም። ይልቁንም ተዓምራዊ ለውጥ አይተናል።
አንድ ኪሎ ምስር 80 ብር ከመግዛት በላይ ተዓምራዊ ለውጥ ከየት ይመጣልናል?
ምስርን ከድሃ ቀለብነት ወደ ሀብታም ምግብነት ያሸጋገርክ ትራንስፎርሜሽን በሁለተኛው አምስት አመትህስ ምን ታመጣ ይሆን?
በሉ ለክፉም ለደጉም እንኳን አደረሳችሁ!
መሰንበት ደግ ነው።