በኢትዮጵያ መንግስት ደህንነቶች ታፍነው ለእስር የበቁት የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን ከፓርቲው ማግለላቸውን በፌስቡክ ገጻቸው ያስታወቁትን አቶ ዮናታን ተስፋዬን ጨምሮ አራት አባሎቹን ፓርቲው ማሰናበቱን ካስታወቀ በኃላ ውዝግቦች መከሰት ጀምረዋል።
ፓርቲው ከጥር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ አቶ ዮናታን ተስፋዬን፣ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑትን አቶ እያስፔድ ተስፋዬን፣ አቶ ጋሻዬነህ ላቀና አቶ ዮናስ ከድርን የድርጅቱን መተዳደሪያ ደንብ ተላልፈው በመገኘታቸው፣ ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከፓርቲው እንዲወገዱ ማድረጉን ገልጿል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ የብሔራዊ ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ ኃላፊ ሃና ዋለልኝ ፊርማ የተላለፈው ውሳኔ እንደሚያስረዳው፣ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 42(5) ሥር ከባድ የሥነ ሥርዓት ቅጣት ስለሚያስከትሉ ጥፋቶች ተደንግጓል፡፡ የፓርቲውን ዓላማ፣ ፕሮግራምና ፖሊሲ መፃረር አይቻልም፡፡ በመሆኑም የተጠቀሱት አባላት ደንቡን በመተላለፋቸው ቅጣቱ እንደተላለፈባቸው አስታውቋል፡፡
አቶ ዮናታን በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ የታሪክና የጎሳ ጥላቻ ያላቸው ቅስቀሳዎችን በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና የተለያዩ የአገሪቱን ቀደምት መንግሥታት ታሪኮች ያጎደፈ፣ ለጥላቻ የሚያነሳሳ፣ በሕዝብ መካከል የባህል መከባበር እንዳይኖር የጥላቻ ቅስቀሳ ማድረጋቸውን ፓርቲው በውሳኔው አስታውቋል፡፡ ሌሎቹም የተሰናበቱት አባላት ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸማቸውን በማብራራት ከፓርቲው መሰናበታቸውን ገልጿል ሲል ሪፖርተር ጋዜጣ ካስነበበ ከቀናት በኃላ የፓርቲው ልሳን የሆነው ነገረ ኢትዮጵያ በሪፖርተር ላይ የወጣው ዜናን ትክክልኝነት አረጋግጧል።
ሀሳብን በነጻነት በመግለጹ በመንግስት እስርና ከፓርቲው የተባረረው ወጣቱ ፖለቲከኛ ዮናታን ተስፋዬ በፌስ ቡክ በፃፋቸው ፅሁፎች መባረሩን ነገረ ኢትዮጵያ አረጋግጧል።
በሰማያዊ ፓርቲ ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ተቋቁሞ የዲሲፕሊን ጉዳዮችን እያየ እንደሚገኝ የተገለጸው የፓርቲው የብሄራዊ ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ አራት የሰማያዊ አባላት ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ባሰራጯቸው ጽሁፎች ‹‹የፓርቲውን ዓላማ፣ ፕሮግራምና ፖሊሲ ጥሰዋል…›› በሚል ህዳር 21/2008 ዓ.ም በብሄራዊ ምክር ቤቱ የቀረበለትን ክስ [ከሳሽ ብሄራዊ ምክር ቤቱ እንደሆነ የም/ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ይድነቃቸው ከበደ አረጋግጠዋል] መርምሮ ጥር 2/2008 ዓ.ም አራቱም ከፓርቲው መባረራቸውን አስታውቋል፡፡
የፓርቲው ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ አባላት ብዛት ሰባት ቢሆኑም ውሳኔው ላይ ስማቸው የሰፈሩት አራቱ ብቻ፣ ማለትም ሀና ዋለልኝ፣ ሻምበል ካሳሁን ተገኘ፣ አቶ ሀሰን ቡሲር እና አቶ ሲሳይ ካሴ ናቸው፡፡ የኮሚቴው ሰብሳቢ ሀና ዋለልኝ፣ ውሳኔው ላይ የተዘረዘሩትና ውሳኔውን ያሳለፉት 4 ስለሆኑ ውሳኔ ለማሳለፍ ኮረም ሞልቷል ስትል ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጻለች ሲል ዘግቧል።
‹‹አራት የኮሚቴው አባላት በጉዳዩ ላይ ተወያይተናል፡፡ ተከሳሾችም መልስ እንዲሰጡን በተደጋጋሚ ጠይቀናቸዋል፡፡ ዮናስ ከድርና እያስጴድ ተስፋየ ክሳቸውን ወስደዋል፤ ሌሎቹ ሁለቱ ግን አልወሰዱም፡፡ ዮናስ መልስ ሳይሆን ወደክስ የሄደበትን ሂደት ተቃውሞ ጽፎልናል፡፡ ዮናታን ተስፋየና ጋሻነህ ላቀ ክሳቸውን አልወሰዱም፤ መልስም አልሰጡንም፡፡ ስለዚህ በክሱ ላይ አንዳቸውም መልስ አልሰጡንም›› ብላለች ሰብሳቢዋ ያለው ነገረ ኢትዮጵያሰብሳቢዋ የኮሚቴው አባላት ኮረም መሙላቱን አረጋግጠን (አራት ሰዎች ተስማምተናል፣ ፈርመናልም በማለት) ነው የወሰነው ብትልም አራተኛው የኮሚቴው አባል አቶ ሲሳይ ካሴ ግን አልተስማማሁም፣ ቃለ-ጉባኤው ላይም አልፈረምኩም ይላል፡፡ ‹‹ጉዳዩን ተወያይተንበታል፤ ክስ ቀርቦልን ክሱን ስናይ ቆይተናል፡፡ ነገር ግን በውሳኔው ላይ ቅሬታ አለኝ፤ ኮሚቴው ውሳኔውን ተስማምቶና ቃለ-ጉባኤ ሳይፈራረም ውሳኔ መሰጠቱንና ውሳኔው ለተሰጠባቸው ሰዎች መድረሱን ሰማሁ፡፡ ቃለ ጉባኤ አልፈረምንም፤ ውሳኔውን ተስማምተን አላጸደቅነውም፡፡ በግሌ በፊርማ አላረጋገጥኩም፡፡ ስለዚህ በሂደቱ ነበርኩ፣ ነገር ግን ውሳኔው ላይ ተስማምቼ በፊርማ አላረጋገጥኩም›› በማለት በውሳኔው ላይ አለመስማማቱንና ውሳኔውን በፊርማው አለማረጋገጡን ለነገረ ኢትዮጵያ አስረድቷል፡፡
ከፓርቲው እንዲሰናበቱ ውሳኔ የተላለፈባቸው አቶ እያስጴድ ተስፋየ እና አቶ ዮናስ ከድር ጥቅምት 14/2008 ዓ.ም ጉዳያቸው ወደ ዲሲፕሊን ተመርቷል የተባለበት የብሄራዊ ም/ቤቱ ስብሰባ በስብሰባው መካፈል የሌለባቸው ሰዎች የተካፈሉበትና ድምጽ የሰጡበት ህገ-ወጥ ስብሰባ ስለነበር ክስ ተመስርቶብናል ብለን እንኳ አናምንም ብለዋል፡፡ ነገረ ኢትዮጵያ ባደረገችው ማጣራት በወቅቱ ስብሰባው ላይ ተገኝተው ድምጽ ከሰጡት መካከል አቶ እንዳሻው እምሻው የም/ቤቱ አባል አለመሆናቸውን ተገንዝባለች፡፡
አቶ እያስጴድ እና ዮናስ ‹‹አሁንም የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ብቻ ሳንሆን፤ የፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት አባላትም ነን›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
በተጨማሪም ‹‹የዲሲፕሊን ክሱ ይመስረትባቸው ከተባለበት ቀን አንጻር የክስ ቻርጁ የደረሰንም ሆነ ውሳኔው የተሰጠበት ጊዜ አሁን እየተደረገ ያለውን ሀገራዊ ትግል ወደኋላ ለመጎተትና ለመከፋፈል በሚፈልጉ ሰዎች የተቀነባበረ ሴራ ነው›› ሲሉ አቶ እያስጴድና አቶ ዮናስ ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው የመባረር ውሳኔ የተላለፈበት አቶ ጋሻነህ ላቀ ደግሞ ‹‹በጊዜ እጥረት ምክንያት ክሱን ባልወሰድኩበትና መልስ ባልሰጠሁበት ሁኔታ የተላለፈብኝ ውሳኔ ነው፡፡ ውሳኔውም በጻፍኩት ጽሁፍ ሳይሆን ሌላ ዓላማ ተይዞ ነው የተባረርኩት›› ብሏል፡፡
በእስር ላይ የሚገኘው አቶ ዮናታን ተስፋየን በተመለከተ የኮሚቴው ሰብሳቢ ሀና ዋለልኝ ጉዳዩን እንደተወያዩበት ትገልጻለች፡፡ ‹‹በኮሚቴው ውስጥ የህግ ባለሙያዎች አሉ፤ የዮናታንን ጉዳይ አንስተን ተነጋግረናል፡፡ በእስር ላይ ሆኖ ውሳኔ መሰጠት ይችላል ወይ የሚለውን አይተነዋል፡፡ በኛ በኩል ዮናታን ከፓርቲው እንደለቀቀ ነው ያገኘነው መረጃ የሚያመለክተው፡፡ ሆኖም ጥፋቱን የፈጸመው የፓርቲው አባል ሳለ ስለሆነ ውሳኔውን ሰጥተናል›› ብላለች ሰብሳቢዋ፡፡
ሰብሳቢዋ ሀና ዋለልኝ ይህን ትበል እንጂ የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ጋሻው መርሻ ግን አቶ ዮናታን ተስፋዬ ከነበረበት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊነት ቦታ እንጂ ከሰማያዊ ፓርቲ አባልነት አለመልቀቁን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጹዋል፡፡ ‹‹ዮናታን ተስፋዬ የፓርቲያችን አባል ነው›› ሲልም ያረጋግጣል አቶ ጋሻው፡፡ ፓርቲው በቅርቡ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እና በተደጋጋሚ ስለ ዮናታን እስር የተጠየቁት የፓርቲው አመራሮችም የዮናታንን አባልነት ጥያቄ ውስጥ ሳያስገቡ የፓርቲያቸው አባል እንደሆነ ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
አቶ ዮናታን ተስፋዬ ከታህሳስ 18/2008 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ መሆኑ እየታወቀ ጥር 2/2008 ዓ.ም (መልስ መስጠትና ራሱን መከላከል በማይችልበት ሁኔታ) ከፓርቲው የመሰናበት ብይን እንደተላለፈበት የገለጸው ነገረ ኢትዮጵያየሰማያዊ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ በአራት አባላቱ ላይ የብሄራዊ ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ ያስተላለፈውን ከፓርቲው የማሰናበት ውሳኔ እንደማይቀበለው ማስታወቁንም ዘግቧል።
የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ዛሬ ጥር 9/2008 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ባካሄደው ስብሰባ አቶ ዮናታን ተስፋየ፣ አቶ እያስጴድ ተስፋየ፣ አቶ ዮናስ ከድር እና አቶ ጋሻነህ ላቀ ላይ የተላለፈውን ውሳኔውንም ሆነ ሂደቱን እንዳልተቀበለውና ውሳኔውም በሰማያዊ ደንብ መሰረት ተግባራዊ እንደማይሆን፣ ተባረሩ የተባሉት አባላትም በሙሉ ኃላፊነታቸው እንደሚቀጥሉ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን የሰማያዊ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
‹‹የተላለፈው ውሳኔ የሰማያዊን መሰረታዊ ሀሳቦችና እምነቶች፣ ማለትም ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትና የግለሰብን ነጻነት የተጋፋ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም›› ብለዋል ሊቀመንበሩ፡፡
የክስ አቀረራረቡም ሆነ የውሳኔ አሰጣጡ በሰማያዊ ደንብ መሰረት ምላዕተ-ጉባኤ ሳይሟላና ቃለ ጉባኤ ሳይፈረም የተሰጠ ውሳኔ በመሆኑ ውሳኔው ተቀባይነት የለውም ሲል ስራ አስፈጻሚው በሙሉ ድምጽ መወሰኑን ኢ/ር ይልቃል አስረድተዋል፡፡የፓርቲው አመራሮች መሀል የተፈጠረው ውዝግብ ፓርቲውን ለሁለት እንዳይከፍለው ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች እየገለጹ ነው።
↧
ሀሳብን በነጻነት በመግለጹ በመንግስት የታሰረውና ከሰማያዊ የተባረረው ወጣቱ ፖለቲከኛ ዮናታን ተስፋዬ ላይ የተላለፈበት ውሳኔ እያወዛገበ ነው።
↧